New Draft By-law

-----

ካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ
ማኅበር

 

ሕገ ማኅበር

ምዕራፍ አንድ

ትርጓሜ

ክፍል 1

1.1  በዚህ ሕገ ማኅበር፣ መተዳደሪያ ደንብ እና በሌሎች ተያያዥ የማኅበሩ ሠነዶች፣ ‹‹ማኅበሩ›› ማለት ‹‹ካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር›› ማለት ነው።

1.2  መተዳደሪያ ደንብ›› በዚህ ሠነድ ስለ እያንዳንዱ ክፍል አግባብነት ያላቸውን ዝርዝር ድንጋጌዎች የያዙ እና የዚህ ሕገ ማኅበር ደጋፊ ተደርገው የሚወሰዱት ናቸው፡፡

1.3  በዚህ ሕገ ማኅበር፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን›› ማለት በትዉልድ ወይም በአሁኑ ጊዜ ዜግነታቸው በምሥራቅ አፍሪካ ከምትገኘው ኢትዮጵያ ከምትባለው አገር የሆኑ ወይም ከእነርሱ የተወለዱ፣ በአሁኑ ወቅት በካልጋሪ እና በአካባቢው በቋሚነት ኗሪ የሆኑ ሰዎች ማለት ነው።

1.4   ‹‹ሙሉ አባል›› ማለት በዚህ ሕገ ማኅበር በክፍል 5 አንቀጽ 5.4 በተጻፈው መሠረት በመልካም የአባልነት አቋም ላይ የሚገኝ ማንኛውም አንድ ወይም ጠቅላላውን ኢትዮጵያውያን አባላት ማለት ይሆናል፡፡

1.5   ‹‹ተባባሪ አባል›› ማለት በትውልድ ኢትዮጲያዊ ያልሆነ ነገር ግን በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ጋብቻን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ትስስር ያለው፣ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦችዋን የሚወድ፣ በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ወስጥ ለመሳተፍ የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ማለት ነው።

1.6  ‹‹ማንኛውም አባል›› ማለት ሙሉ አባል ወይም ተባባሪ አባል ማለት ነው።

1.7   “ቦርድ›› ማለት በጠቅላላ ጉባኤው የሚመረጥ የአመራር አካል ማለት ነው

1.8   የሥራ አስፈጻሚው አካል›› ማለት ከቦርዱ አባል ዉስጥ ለዕለት ተዕለት ስራ ለማከናወን የሚመረጡ ግለሰቦችን ማለት ነው።

1.9  ሕግ›› ማለት በዚህ ሠነድ እንደተጠቀሰው የአልበርታ የማኅበራት ሕግ ማለት ሲሆን እንደዚህ ባለው ሕግ ላይ

ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚደረጉ ማሻሻያዎች በዚህ ትርጓሜ ሥር የሚካተቱ ይሆናሉ።

1.10  ዋነኛ ድርጊቶች›› ማለት ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው የፋይናንስ እና/ወይም ከፋይናንስ ውጭ የሆኑ የግብዓት ግዴታዎች አንጻር ማኅበሩ ግዴታ ሊገባባቸው የሚችልባቸው ጉዳዮች ማለት ይሆናል፡፡

 

ምዕራፍ ሁለት

ስም፤ ዓላማ፤ አርማ፤ ማኅተምና ቋንቋ

ክፍል 2

ስም ዓላማና ዓርማ

2.1.  የማኅበሩ ስም ‹‹ካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህ ሠነድ ‹‹የካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር ሕገ ማኅበር 2020›› በመባል ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2.2. የካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት ከጎሣና ከፆታ ክፍፍል ነጻ የሆነ ድርጅት ነው፣

2.3. የማኅበሩ ዓላማ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ያካትታል፡-

2.3.1. በካልጋሪ እና በአካባቢው ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ የጋራ ደኅንነት እና ጥቅሞች ለማስጠበቅ መሥራት፣

2.3.2. በሕዝብ መድረኮች እና በማኅበረሰብ የልማት መርሐ ግብሮች የአባላቱን የጋራ ጥቅሞች መወከል እና

ማጎልበት፣

2.3.3. የኢትዮጵያን ባሕል እና ማኅበራዊ እሴቶች ግንዛቤ በካናዳ ማህበረሰብ ዘንድ በሰፊው ማዳበር፣

2.4. ማህበሩ የራሱ የሆነ ዓርማ ይኖረዋል። የማህበሩ ዓርማ በጠቅላላ ጉባኤዉ ይወሰናል።

 

ክፍል 3

የማኅበሩ ማኅተም

 

3.1.  የማኅበሩ ማኅተም በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የማኅበሩ ስያሜና አርማ የሚቀረጽበት ሲሆን በቦርዱ በጸደቀው አኳኋን ይዘጋጃል፡፡

3.2. የማኅበሩ ጸሐፊ የማኅበሩን ማኅተም በኃላፊነት ይይዛል፤ ማኅተሙ ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ ሁሉ የፕሬዚዳንቱ

ፊርማ ወይም ፕሬዚዳንቱ በማይኖርበት ጊዜ የገንዘብ ያዡ ፊርማ መስፈር ይኖርበታል፡፡

 

 

ክፍል 4

ቋንቋ እና አተረጓጎም

 

4.1.  በዚህ ሕገ ማኅበር እንዲሁም ተያያዥነት ባላቸው የመተዳደሪያ ደንብ ሠነዶች በተባእት ወይም በነጠላ የተገለጸ ቢኖር አንስታይ ወይም ብዙ ቁጥርን፣ በአንስታይ እና በብዙ ቁጥር የተገለጸ ደግሞ ተባእት እና ነጠላ ቁጥርን የሚያካትት ይሆናል፡፡

4.2. አማርኛ የማኅበሩ የሥራ ቋንቋ ሲሆን እንግሊዝኛ ቋንቋ ደግሞ ለውጭ ግንኙነት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ሆኖም ግን ማንኛውም የማኅበሩ አባል በማናቸውም በኢትዮጵያ ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች ከማኅበሩ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ቢፈልግ ማኅበሩ የአባሉን ጥያቄ ለማስተናገድ የተቻለውን ጥረት ሁሉ ያደርጋል፡፡

4.3. ይህ ሕገ ማኅበር  በጠቅላላ ጉባኤው ከፀደቀ በኋላ ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በአልበርታ ሬጅስትራር ይመዘገባል። በአልበርታ ፍርድ ቤት ሂደት ዉስጥ በዚህ ሕገ ማኅበርና በእንግሊዘኛው ትርጓሜ መካከል ቅራኔ ከተፈጠረ የእንገሊዘኛው ቋንቋ የፀና ይሆናል።

4.4. ማኅበሩ ከውጭ  አካላት  ጋር  በሚያደርገው ግንኙነት  አግባብነት  ያላቸውን  ሠነዶች  እንዲሁም የፋይናንስ

መግለጫዎችንና መዝገቦች እንደአስፈላጊነቱ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲተረጎሙ እና እንዲቀመጡ ያደርጋል፡፡

 

ምዕራፍ ሦስት

አባልነት

ክፍል 5

የሙሉ አባልነት መስፈርት

 

 

5.1.  አመልካቾች ለአባልነት ብቁ ለመሆን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ማሟላት ይኖርባቸዋል፡

5.1.1.  ዕድሜያቸው ቢያንስ 18 ዓመት የሆነና በካናዳ ቋሚ ኗሪ የሆኑ ወይም በካናዳ ቢያንስ ለ3 ወራት በሕጋዊ ኗሪነት የቆዩ ኢትዮጵያዊያን መሆን አለባቸው ፤

5.1.2. በካልጋሪ ከተማ እና/ወይም በአካባቢው ቢያንስ ለ3 ወራት ኗሪ የሆኑ መሆን አለባቸው፤

5.1.3. የማኅበሩን ዓላማዎች እና ተልእኮ ለመደገፍ ጊዜያቸውን እና ጥረታቸውን በበጎ ፈቃደኝነት ለማበርከት የሚስማሙ መሆን አለባቸው፣

5.2. ለሙሉ አባልነት ብቁ የሆነ ማናቸውም ሰው በዚህ ሕገ ማኅበር መሠረት በሥራ አስፈጻሚው አካል የተዘጋጀውን

ቅጽ በመሙላት ለአባልነት ማመልከት ይኖርበታል፡፡

5.3. እያንዳንዱ አባል በጠቅላላ ጉባኤው በተወሰነው መሠረት የምዝገባ እና የአባልነት ክፍያዎችን ለማኅበሩ ገንዘብ ያዥ መክፈል ይኖርበታል፡፡

5.4. ማንኛውም የማኅበሩ ሙሉ አባል የአባልነት ክፍያዉን በመክፈል እና የማህበሩን ሕገ ማህበር በመቀበል በማኅበሩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል፡፡

 

ክፍል 6

የተባባሪ አባልነት መስፈርት

6.1 አመልካቾች ለአባልነት ብቁ ለመሆን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ማሟላት ይኖርባቸዋል፡

6.1.1. ዕድሜያቸው ቢያንስ 18 ዓመት የሆነና በካናዳ ቋሚ ኗሪ የሆኑ ወይም በካናዳ ቢያንስ ለ3 ወራት በሕጋዊ ኗሪነት የቆዩ መሆን አለባቸው፤

6.1.2. በካልጋሪ ከተማ እና/ወይም በአካባቢው ኗሪ የሆኑ መሆን አለባቸው፤

6.1.3. የማኅበሩን ዓላማዎች እና ተልእኮ ለመደገፍ ጊዜያቸውን እና ጥረታቸውን በበጎ ፈቃደኝነት ለማበርከት የሚስማሙ መሆን አለባቸው፣

6.2.   ለተባባሪ አባልነት ብቁ የሆነ ማናቸውም ሰው በዚህ ሕገ ማኅበር መሠረት በሥራ አስፈጻሚው አካል የተዘጋጀውን ቅጽ በመሙላት ለተባባሪ አባልነት ማመልከት ይኖርበታል፡፡

6.3.   እያንዳንዱ ተባባሪ አባል በጠቅላላ ጉባኤው በተወሰነው መሠረት የምዝገባ እና የተባባሪ አባልነት ክፍያዎችን ለማኅበሩ ገንዘብ ያዥ መክፈል ይኖርበታል፡፡

6.4.   ማንኛውም የማኅበሩ ተባባሪ አባል የተባባሪ አባልነት ክፍያ በመክፈል እና የማህበሩን ሕገ ማህበር በመቀበል

በማኅበሩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል፡፡

 

 

ክፍል 7

እግድ፣ ከአባልነት መሰናበት እና አባልነትን መልሶ ስለማግኘት

7.1.  ማንኛውም አባል ከማኅበሩ አባልነት መልቀቅ ሲፈልግ ፍላጎቱን በጽሑፍ ለማህበሩ ፅህፈት ቤት በማሳወቅ ከአባልነት መሰናበት ይችላል፡፡

7.2. ማንኛውም አባል ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የአባልነት ክፍያውን ካልከፈለ ከአባልነት ታግዶ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ አባሉ ወደ አባልነት አቋሙ እስኪመለስ ድረስ ማናቸውም የአባልነት መብት/ሥልጣን አይኖረውም፡፡

7.3. ቦርዱ ማንኛውንም የማኅብሩን አባል ለሦስት ወራት ከማኅበሩ ሊያግድ ይችላል፡፡ ይህ ተፈጻሚ የሚሆነው ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ምክንያቶች እና ከቦርዱ አባላት መካከል ሁለት ሶስተኛዉ በሆኑት ሲደገፍ ይሆናል፡፡

7.3.1. ሕገ ማኅበሩን አለማክበር፤

7.3.2. የማኅበሩን ስብሰባ፤ እንቅስቃሴና አገልግሎት ማወክ፤

7.3.3. ለማኅበሩ ጎጂ በሆነ ድርጊት ውስጥ ተሣታፊ ሆኖ መገኘት፣

አባሉ ከሦስት ወራት ዕገዳ በኋላ ከላይ የተዘረዘሩትን ድርጊቶች በድጋሚ ከፈፀመ ቦርዱ እስከሚቅጥለው ጠቅላላ ስብሰባ ድረስ ከማህበሩ ሊያግድ ይችላል።

7.4. ማንኛውም አባል የማኅበሩ ጠቅላላ ስብሰባ አግባብ ነው ብሎ ባመነበት ማናቸውም ምክንያት እና በ2/3ኛ አብላጫ ድምፅ ከአባልነቱ ሊሰረዝ ይችላል፡፡ ማንኛዉም አባል ይህ ዉሳኔ ከመሰጠቱ በፊት በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ በተመለከተው መሠረት ተወካይ ይዞ አቤቱታ የማቅረብ መብት ይኖረዋል።

7.5. ማንኛውም ከአባልነት የተሰረዘ አባል ከሁለት ዓመታት በኋላ የአባልነት ማመልከቻ በፅሁፍ በድጋሚ ማቅረብ

ይችላል፡፡ ቦርዱ ጉዳዩን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል፡፡

ምዕራፍ አራት

ድርጅታዊ መዋቅር

 

ክፍል 7

7.1.  ማኅበሩ የሚከተሉት አካላት ይኖሩታል ሀ.   ጠቅላላ ጉባኤ

ሀ.   ጠቅላላ ጉባኤ

ለ.   ቦርድ

ክፍል 8

ጠቅላላ ጉባዔ

8.1.  ጠቅላላ ጉባዔው የማኅበሩ ከፍተኛ ፖሊሲ አውጪ እና ውሳኔ ሰጪ አካል ነው፡፡ ክፍል 9

 

ክፍል 9

ቦርድ

 

9.1.  ቦርዱ የማኅበሩን ንብረት በበላይ የሚጠብቁና የማኅበሩን አጠቃላይ ደኅንነትና የሥራ እንቅስቃሴ በበላይነት የሚቆጣጠሩ ሰባት ተመራጭ አባላትን ያካትታል፡፡

9.2. የቦርዱ አባላት በጠቅላላ ጉባዔው ይመረጣሉ፡፡ ቦርዱ ከተመራጮቹ አባላት መካከል ሶስት የሥራ አስፈጻሚ

አካል አባላትን ለፕሬዚዳንትነት ለጸሐፊነትና ገንዘብ ያዥነት ይመርጣል፡፡ የአንድ የቦርድ አባል የሥራ ዘመን ሁለት ዓመት ይሆናል።

9.3. የቦርድ አባል ምርጫ በየሁለት ዓመቱ ይካሄዳል።

9.4.  የማኅበሩ የአመራር ለዉጥ ስርዓት የያዘና ሽግግሩ ቀና ይሆን ዘንድ የምርጫው ፕሮግራም እንደሚከተለው ይከናወናል

9.4.1. ይህ ህገ ማህበር በፀደቀበት መጀመሪያው ዓመት ሰባት የቦርድ አባላት ይመረጣሉ

9.4.2. በሚቀጥሉት ሙሉ ቁጥር የምርጫ ጊዜ 4 እና ጎዶሎ ቁጥር የምርጫ ጊዜ 3 የቦርድ አባላት ይመረጣሉ

9.4.3. በሁለተኝው የምርጫ ጊዜ ብቻ ለሥራ አስፈጻሚ አካልነት ያልተመረጡት አራት የቦርድ አባላት ምርጫው ላይ አይወዳደሩም። ሶስቱ የሥራ አስፈጻሚ አካል አባላት ለድጋሚ ምርጫ መሳተፍ ይችላሉ

9.4.4. የሥራ አስፈፃሚ አባል አካላት በየሁለት አመቱ ከቦርዱ ዉስጥ ይመረጣሉ

9.5. የቦርዱ አባላት በአልበርታ የማኅበራት ሕግ መሠረት አግባብነት ባለው ምዝገባ ጽ/ቤት (ሬጂስትራር) ዘንድ ተመዝግበው በመተዳደርያ ደንቡ በተሰጣቸው ኃላፊነትና የሥራ ድርሻ ዝርዝር መሠረት ተግባራቸውን ያከናውናሉ፡፡

9.6. ቦርዱ በአጠቃላይ የማኅበሩን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በተመለከተ ኃላፊነት ባይኖርበትም በዚህ ሕገ ማኅበር በክፍል 14 መሠረት የተወሰኑ ጉዳዮችን አስመልክቶ ውሳኔ የመስጠት ድርሻ ይኖረዋል፡፡

9.7. ቦርዱ የማኅበሩን ዓመታዊ በጀት እና የሥራ እቅድ የማጽደቅ ሥልጣንና ኃላፊነት አለው፡፡ ከዚህም ሌላ ቦርዱ በጸደቀው በጀት/የሥራ እቅድ በግልጽ ያልተቀመጡ ሌሎች ዋነኛ ድርጊቶችና እንዲሁም በማኅበሩ ዓላማዎች እና የወደፊት አቅጣጫ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ይኖረዋል፡፡

9.8. ከቦርዱ መካከል የ66 በመቶ ድጋፍ ካገኘ አንድን የቦርድ አባል በሕገ ማኅበሩ በተጠቀሰው መሠረት ለ3ወር ጊዜ ከስራ ሊያግድ ይችላል፡፡ ሆኖም የቦርዱ አባል በድጋሚ ችግር ከተገኘበት እስከሚቀጥለው ጠቅላላ ስብሰባ ድረስ ቦርዱ ከስራ ሊያግድ ይችላል፡፡

9.9. ቦርዱ በራሱ በቦርዱ አባላት ላይ የቀረበን አግባብነት ያለው ማናቸውንም አቤቱታ ሊመረምር እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከውሳኔ ሐሳብ ጋር የምርመራውን ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባዔ ሊያቀርብ ይችላል፡፡

9.10. የሥራ አስፈጻሚ አካል አባላት ማለትም ፕሬዚዳንቱ፣ ጸሐፊው፣ ወይም ገንዘብ ያዡ በገዛ ፈቃዳቸው ሲለቁ ወይም ከኃላፊነታቸው ሲነሡ ክፍት የሆኑት የኃላፊነት ቦታዎች በልዩ ጠቅላላ ስብሰባ በተቻለ ፍጥነት እስኪሟሉ ድረስ ቦርዱ የሚከተለውን ይፈጽማል፡፡

9.10.1. አስተዳደሩንና የንብረት ቁጥጥርን በኃላፊነትን ይመራል፡፡

9.10.2.  ክፍት ለሆኑ የኃላፊነት ቦታዎች ከቦርድ አባላቱ መካከል በጊዜያዊነት ይመድባል፡፡

9.10.3.  በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ይሠሩ ለነበሩ አባላት የሥራ መልቀቂያ ማስረጃ በይፋ ከመስጠቱ በፊት/ወዲያውኑ ኦዲት እንዲካሄድ ያደርጋል፡፡

9.10.4.  ከማኅበሩ ከኃላፊነት ቦታ የተነሡ አባላት ያላቸውን በቼክ በባንክና በሌሎች የማህበሩ ሠነዶች ላይ የመፈረም ሥልጣን ይሰርዛል፣ ለሚመለከታቸው ባንኮችና የመንግስት አካላት ወዲያውኑ ያሳውቃል፡

9.10.5.  ከማኅበሩ ከኃላፊነት ቦታ የተነሡ አባላትን በአልበርታ የማኅበራት ሕግ መሠረት አግባብነት ባለው ምዝገባ ጽ/ቤት (ሬጂስትራር) ዘንድ ስማቸዉን ያሰርዛል

9.10.6.  የመፈረም ሥልጣን የማኅበሩን የዕለት ተዕለት ሥራዎች ለማካሄድ ያህል ብቻ (በመተዳደሪያ ደንቡ

መሠረት) ተፈጻሚ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

9.11. ማናቸውም የቦርድ አባል ከሁለት ተከታታይ ጊዜ በላይ ሊመረጥ አይችልም፡፡

9.12. ሁለት ተከታታይ የኃላፊነት ጊዜያትን ያጠናቀቀ የቦርድ አባል ቢያንስ ለሁለት ዓመት ያህል ለቦርድ አባልነት መወዳደር አይችልም፡፡

 

ክፍል 10

ሥራ አስፈጻሚ አካል

10.1.  ሥራ አስፈፃሚው አካል የማኅበሩን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እና ጉዳዮችን የሚመራና የሚያካሂድ አካል ሲሆን፣ በዚህ ሕገ ማኅበር፣ በመተዳደሪያ ደንቡ እና በሌሎች ተያያዥነት ባላቸው ሠነዶች እና አሠራር መሠረት ማኅበሩን በመወከል እና በማኅበሩ ስም የማኅበሩን ሥልጣን ይጠቀማል፡

10.2. ሥራ አስፈጻሚው አካል ከቦርድ አባላት መካከል ከተመረጡት አባላት በተጨማሪ ለተለያዪ የሥራ ሃላፊነት ብቃት አላቸው ብሎ ያመነባቸዉን    አባሪ ዕጩ ግለሰቦችን ከማንኛውም አባል መርጦ ለቦርዱ አቅርቦ ያፀድቃል።

10.3. የሥራ አስፈፃሚው አካል አባላት በዚህ ሕገ ማኅበር እና በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት ለሁለት ዓመት ጊዜ ከቦርዱ አባላት ዉስጥ ይመረጣሉ፡፡ማንኛውም የሥራ አስፈጻሚው አካል ከሁለት ተከታታይ ጊዜያት በላይ ሊመረጥ አይችልም፡፡

10.4. ሥራ አስፈፃሚው አካል የማኅበሩ ንብረቶችን የማስተዳድር ኃላፊነት አለበት፡፡ እነዚህንም ንብረቶች በአልበርታ ክፍለ ግዛት ሕግጋት በካልጋሪ ከተማ መተዳደሪያ ሕግ እንዲሁም ከቦርዱ በየጊዜው በሚወጡ የሥራ አመራር ፖሊሲዎች እና አሠራር መሠረት የማስተዳደር ግዴታ ይኖርበታል፡፡

10.5. የሥራ አስፈፃሚው አካል ዓመታዊ በጀትንና ዋና ዋና የሥራ እቅድን አዘጋጅቶ በቦርዱ እንዲፀድቅ ያደርጋል። የማኅበሩን ተለዋዋጭ ድርጅታዊ የሥራ ፍላጎት በመለየት የፖሊሲ አፈጻጸምን ያዳብራል፣ ያዘጋጃል፡፡

10.6. ሥራ አስፈፃሚው አካል ተገቢ የሥራ አመራርና የማህደር አያያዝ ፖሊሲና አፈጻጸም በመቅረጽ ሥራ ላይ የማዋል ኃላፊነት አለበት፡፡

10.7. ሥራ አስፈፃሚው አካል በክፍል 11 መሠረት ቋሚና ጊዜያዊ ንዑሳን ኮሚቴዎችን ያዋቅራል፣ አባላትንም

ይመድባል፡፡

 

ክፍል 11

ንዑሳን ኮሚቴዎች

11.1. ማኅበሩ በሥራ አስፈጻሚው አካል የሚመረጡ እና ለአካሉ ተጠሪ የሆኑ ጊዜያዊና ቋሚ ኮሜቴዎችን እንደአስፈላጊነቱ ማቋቋም ይችላል፡

11.2. እያንዳንዱ ኮሚቴ በመተዳደሪያ ደንቡ በተዘረዘረውና ከሥራው ጋር አግባብነት ካለው ዓላማ፣ ተግባርና ኃላፊነት አኳያ ሥራውን ያከናውናል፡፡

 

ክፍል 12

የአማካሪዎች ምክር ቤት

12.1. ቦርዱ አስተዳደራዊ ሥልጣን የማይኖረው ከማህበሩ ማንኝዉም አባል የተዉጣጣ የአማካሪዎች ምክር ቤት ሊያቋቁም ይችላል፡፡

12.2. የምክር ቤቱ ተግባር ከዚህ በታች በተዘረዘረው መልክ ለማኅበሩ አመራር ምክር መለገስ ይሆናል፡-

12.2.1. ከማኅበሩ የሥራ አመራር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በቦርዱ በሚሰጥ መመሪያ መሠረት በጋራ ወይም በተናጠል ምክር እና የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት፣

12.2.2.  በባሕላዊ እውቀትና እሴቶች፣አስተዳደር፣ የሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ ምክር እና ውሂብ (ዴታ)

ይሰጣል፡፡

12.3. የምክር ቤቱ አባላት ቁጥርና ስብጥር ቦርዱ በየጊዜው ተገቢ ነው ብሎ በሚወስነው መሠረት ይሆናል፡፡

12.4. የአማካሪዎች ምክር ቤት አባላት ለቦርድ አባላት ቀርቦ በበቂ ምክንያት ካልተወሰነ ወይም በራሳቸው ፍላጎት ከኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ ካላቀረቡ በስተቀር ለአራት ዓመት በአገልግሎት ላይ ይቆያሉ፡፡

 

ምእራፍ አምስት

አመራር እና አስተዳደር

ክፍል 13

አስተዳደር

 

13.1. ቦርዱ በማኅበሩ የሥራ አቋምና እንቅስቃሴ አንዲሁም የሂሳብ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ ቢያንስ በሦስት ወር አንድ ጊዜ መደበኛ ስብሰባ ያካሂዳል፡፡ አብላጫውን ቁጥር የያዙ የቦርድ አባላት በስብሰባው ከተገኙ መደበኛ ስብሰባ ይካሄዳል፡፡ በስብሰባው የተገኙት የቦርድ አባላት ምልዓተ ጉባዔውን የማያሟሉ ከሆነ፣ የተገኙ አባላት በአብላጫ በሚሰጡት ውሳኔ የስብሰባውን ቀን ለሌላ ጊዜ ማራዘም ይቻላል።

13.2. የሥራ አስፈፃሚ አካል ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ መደበኛ ስብሰባዉን ይካሄዳል፡፡

13.3. ፕሬዚዳንቱ በዚህ ሕገ ማኅበር ወይም በመተዳደሪርያ ደንቡ መሠረት በቦርዱ አብላጫ አባላት ጥያቄ ሲቀርብለት የቦርዱን አስቸኳይ ስብሰባ በማናቸውም ወቅት መጥራት ይገባዋል።

13.4. ፕሬዚዳንቱ በዚህ ሕገ ማኅበር ወይም መተዳደሪርያ ደንብ መሠረት በሥራ አስፈፃሚው አካል አብላጫ አባላት ጥያቄ ሲቀርብለት የኮሚቴውን አስቸኳይ ስብሰባ በማናቸውም ወቅት መጥራት ይጠበቅበታል፡፡

13.5. አብላጫ ቁጥር ያላቸው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በማናቸውም የኮሚቴው ስብሰባ ላይ ከተገኙ ስብሰባውን ለማካሄድ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል፡፡ በስብሰባው የተገኙት የሥራ አስፈፃሚው አካል አባላት ምልዓተ ጉባዔውን የማያሟሉ ከሆነ የተገኙ አባላት በአብላጫ በሚሰጡት ውሳኔ የስብሰባውን ቀን ለሌላ ጊዜ ማራዘም ይቻላል፡፡

13.6. ማንኛዉም ስብሰባ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት መሰረት ይካሄዳል፡፡

13.7. የሥራ አስፈፃሚ አካል አባላት በድምፅ ብልጫ መወሰን ያልቻሉትን ማንኝዉም ጉዳዮች ለቦርዱ አቅርበው ያስወስናሉ።

13.8. ማኅበሩ ኃላፊነታቸውንና ልዩ መብታቸውን እንዲሁም የማኅበሩን ንብረቶች ያለአግባብ በሚጠቀሙ የቦርድ አባላት ላይ የሥነ-ሥርዓት እና/ወይም ሕጋዊ እርምጃዎች የመውሰድ መብት አለው፡፡

 

ክፍል 14

የቦርድ ስብሰባ

14.1. ቦርዱ በአጠቃላይ ማለትም የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በጋራ ሊታዩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት በሚያካሂዱት የቦርድ ስብሰባ ላይ የሚወሰኑት ጉዳዮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-

14.1.1. ከቦርድ አባላት ዉስጥ በክፍል 10.2 መሰርት የሥራ አስፈፃሚ አካል አባላትን መምረጥ

14.1.2. ረቂቅ ዓመታዊ በጀትንና ዋና ዋና እቅዶችን ማጽደቅ

14.1.3.  ከሥራ አስፈፃሚ አካል በየሩብ ዓመቱ የሚቀርበዉን የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት መገምገም እና ማጽደቅ

14.1.4. የሥራ አስፈፃሚ አካል አባሪ አባላትን ምርጫ ማጽደቅ

14.1.5. በቁጥር 13.7 መሰረት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በድምፅ ብልጫ መወሰን ያልቻላቸውን ማንኛዉም ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ዉሳኔ መስጠት

14.1.6. የአስመራጭ ኮሚቴ አባላትን መሰየም

14.1.7. የአማካሪዎች ምክር ቤት አባላትን መምረጥ

14.1.8. ከቦርዱና ከሥራ አስፈፃሚው አካል በመወገድ ወይም በገዛ ፈቃዳቸው በለቀቁ አባላት ምትክ ጊዜያዊ ኃላፊዎችን እስከ ተከታዩ የማኅበሩ ጠቅላ ጉባኤ ድረስ መመደብ

14.1.9. ጠቅላላ ጉባኤዉ የዉጪ ኦዲተሮች ያስፈልጋሉ ብሎ ከወሰነ ኦዲተሮችን መምረጥ

14.1.10. ከማኅበሩ አባላት መካከል ኦዲተሮችን መልምሎ ለጠቅላላ ጉባኤዉ አቅርቦ ማጸደቅ፤

14.1.11. ለጠቅላላ ጉባኤዉ ሊቀርብ የተዘጋጀዉን ዓመታዊ የኦዲት እና ሌሎች ሪፖርቶችን ማጽደቅ

14.2. በቦርድ ስብሰባ የተሰጠ ውሳኔ የሚጸናው በስብሰባዉ ላይ በተገኙ አብላጫ ድምፅ ሲደገፍ ይሆናል፡፡ ዉሳኔዉ፣ የሥራ አመራር አካል አባላት ባልሆኑ፣ ቢያንስ ሁለት የቦርድ አባላት መደገፍ ይኖርበታል።

14.3. የሥራ  አስፈፃሚው  አካል  ፕሬዚዳንት  የቦርድ  ስብሰባዎችን  ይጠራል፣  የሚካሄዱበትን  ጊዜ  ይወስናል፣ ስብሰባዎችን ይመራል፡፡

 

ክፍል 15

በገዛ ፈቃድ ኃላፊነትን መልቀቅ፣ ከኃላፊነት መነሳት እና ክፍት የኃላፊነት ቦታዎች

 

15.1. የቦርዱ አባል የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ በጽሑፍ በመስጠት በገዛ ፈቃዱ ኃላፊነቱን ሊለቅ ይችላል፡፡

15.2. በመደበኛ ወይም ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ በሚሰጥ አብላጫ ድምፅ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት በማናቸውም ምክንያቶች አንድ የቦርድ አባል ከኃላፊነት ሊነሣ ይችላል፡-

15.2.1.   ሕገ ማኅበሩ እና መተዳደሪያ ደንቡን አለማክበር፤

15.2.2.  ማኅበሩን ሊጎዳ በሚችል ተግባር ላይ መገኘት፤

15.2.3.  የኃላፊነት ግዴታን አለመወጣት፤

15.2.4.  በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ ዕጽ ተጽዕኖ ሥር ሆኖ በማኅበሩ ስብሰባዎች መገኘትና ማንኛውንም የማኅበሩን ሥራ ማወክ፤

15.2.5.  ሌሎች የሥራ አስፈጻሚ ወይም የቦርድ አባላትን ስም ማጥፋት፤ ወይም

15.2.6.  የቦርድ አባላትን ሆነ የሥራ አስፈጻሚውን ሥራ ማወክ፤

15.3. በዚህ መልኩ ውሳኔ የተላለፈባቸው የቦርድ አባላት ወሳኔውን በመቃወም አቤቱታ የማቅረብና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ተወካይ ይዞ የመቅረብ መብት ይኖራቸዋል፤

15.4. ጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ የተላለፈባቸውን የቦርዱን አባላት ማብራሪያ በመስማት ስለ አባሉ/አባላቱ ከኃላፊነት መነሣት አስመልክቶ ውይይት በማድረግ ውሳኔ ይሰጣል፤

15.5. በቦርድ የኃላፊነት ቦታዎች በገዛ ፈቃድ በመልቀቅ ወይም በመነሣት ክፍት ቦታ ሲኖር ቦርዱ በክፍል 9.11 መሰረት እስከ ተከታዩ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ የጎደለዉን የስራ ዘርፍ ይሸፍናል፡፡

 

ምዕራፍ ስድስት

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎች

ክፍል 16

ጠቅላላ ደንቦች

16.1. ማኅበሩ ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ እና ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ ይኖሩታል፡፡

16.2. የማኅበሩ ስብሰባዎች እንደየአስፈላጊነቱ ለሕዝብ ክፍት ይሆናሉ፡፡ በስብሰባው የተገኙ አባል ያልሆኑ ሰዎች በስብሰባው ሂደት ላይ በታዛቢነት ብቻ ይሳተፋሉ፡፡

 

16.3. ማንኛውም  ስብሰባ  በፕሬዚዳንቱ  ወይም  በፀሀፊዉ  (ፕሬዚዳንቱ  ከሌለ)  ይመራል፡፡  ሁለቱም  ኃላፊዎች በማይኖሩበት ሁኔታ ከሥራ አመራር አካል አባላት ውስጥ ቦርዱ ሰብሳቢ ይመርጣል።

16.4. የውሳኔ ሐሳብ በተለየ መልክ እንዲጸድቅ አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በስተቀር ድምፅ የሚሰጠው በስብሰባ በተገኙ አባላት አብላጫ ድምፅ ይሆናል፡፡

16.5. በማንኛውም ዓመታዊ ወይም ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ አብላጫ የቦርድ አባላት፣ አንድ የሥራ አመራር አካል አባልና

20 ከመቶ በመልካም የአባልነት አቋም ላይ ያሉ አባላት ምልዓተ ጉባዔ ያሟላሉ፡፡ በመጀመሪያው ሰብሰባ ምልዓተ ጉባዔ ካልሞላ ተለዋጭ ሰብሰባ ይጠራና በተለዋጩ ስብሳባ በተገኘው የቦርድ አባላትና በመልካም የአባልነት አቋም ላይ ባሉ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቁጥር ጉባኤው ሊካሄድ ይችላል። በዚህ ወቅት፣ ፕሬዚዳንቱ እና ፀሀፊዉ ካልተገኙ፣ ሰብሳቢ ከተገኙት የስራ አመራር ወይም የቦርድ አባላት ዉስጥ ይመረጣል።።

16.6. የማኅበሩ ጸሐፊ የስብሰባዎችን ትክክለኛ ቃለ ጉባኤ ይይዛል፡፡ የማኅበሩ ጸሐፊ በስብሰባዉ ላይ ካልተገኘ፣

የስብሰባዉ መሪ የስብሰባ ቃለ ጉባኤ የሚይዝ ጊዜያዊ ጸሀፊ፣ ከሥራ አመራሩ ፣ ከቦርድ አባላት ወይም ከጠቅላላ ጉባኤዉ ሊሰይም ይችላል።

16.7. ስብሰባዎች በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ይመራሉ፡፡

 

 

ክፍል 17

ጠቅላላ ስብሰባ

 

17.1. ማኅበሩ መደበኛ ጠቅላላ ስብሰባውን በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ የሚያካሂድ ሲሆን ለአባላት የስብሰባ ጥሪ በጽሑፍ ወይም በስልክ ወይም በተለያዩ በማህበሩ መገናኛ ዘዴዎች ይደረጋል፡፡

17.2. ማህበሩ የመጀመሪያዉን አመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ስብሰባ ምርጫ ከተካሄደ 13 ወር ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ ማካሄድ ይኖርበታል።

17.3. የጽሑፍ የስብሰባ ጥሪ በአባላቱ በመጨረሻ በሚታወቅ አድራሻ (በደብዳቤ ወይም በኢሜይል) ስብሰባው ከሚካሄድበት ቢያንስ ከ21 ቀናት ቀደም ብሎ ይላካል፡፡ ከስብሰባው ጥሪ ጋር የጠቅላላ መደበኛ ስብሰባው የአጀንዳ ግልባጭ ለአባላት ይላካል፡፡

 

ክፍል 18

ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ

 

18.1. ማኅበሩ የጠቅላላ አባላት ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው አስቸኳይ ጉዳዮችን ለማየትና ለመወያየት ልዩ ጠቅላላ ስብሰባዎችን ያካሂዳል፡፡

18.2. ልዩ ጠቅላላ ስብሰባው ከቦርድ አባላት በአብላጫ ድምጽ በጽሑፍ ሲጠይቁ በማንኛውም ወቅት ሊጠራ ይችላል።

18.3. ከአባላቱ መካከል ላለፈው ሁለት ዓመት በመልካም የአባልነት አቋም ላይ ያሉ 20 ከመቶ የሚሆኑት አባላት በማንኛውም ወቅት በጽሑፍ ከጠየቁ ማኅበሩ ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፡፡

18.4. ለልዩ ጠቅላላ ስብሰባ የሚቀርብ የጽሑፍ ጥያቄ ስብሰባው የተጠራበትን ምክንያትና በስብሰባው ውይይት ሊደረግባቸው የታቀዱ ረቂቅ የውሳኔ ጉዳዮችን መጥቀስና ማካተት ይኖርበታል፡፡

18.5. ቦርዱ ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ እንዲካሄድ ጥያቄ ሲቀርብለት አጀንዳ በማዘጋጀት በአንድ  ወር  ጊዜ ውስጥ ስብሰባውን ይጠራል፡፡ ስብሰባው የተጠራው ከላይ በተራ ቁጥር 18.3 መሰረት ከሆነ የሰብሰባው አጀንዳ ያንኑ ጉዳይ ብቻ የተመለከተ ይሆናል።

18.6. ልዩ ጠቅላላ ስብሰባው ከሚካሄድበት ቢያንስ ከ21 ቀናት ቀደም ብሎ አጀንዳውን ያካተተ እና በጽሑፍ የተዘጋጀ የስብሰባ ጥሪ ለአባላት ለመጨረሻ ጊዜ በሚታወቅ አድራሻ (የመኖሪያ ወይም የኢሜይል) እንዲሁም ማህበሩ በሚጠቀምባቸው የመገናኝ ዘዴዎች ይላካል፡፡

18.7. በልዩ ጠቅላላ ስብሰባው ለውይይት የሚቀርቡትና ውሳኔ የሚተላለፍባቸው ጉዳዮች በስብሰባ ጥሪው አጀንዳ የተካተቱት ብቻ ይሆናሉ፡፡

 

ምእራፍ ሰባት

ምርጫ እና ድምጽ አሰጣጥ

 

ክፍል 19

የአስመራጭ ኮሚቴ

 

 

19.1. ቢያንስ አምስት አባላት ያሉት የአስመራጭ ኮሚቴ በቦርዱ ይሰየማል፡፡

19.2. ኮሚቴው ሰብሳቢ ይመርጣል፡፡

19.3. ኮሚቴው ምርጫውን ለማካሄድ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ከሚካሄድበት ቀን ቢያንስ ከስድስት ሳምንት ቀደም ብሎ ስራዉን መጀመር ይኖርበታል፡፡

19.4. የአስመራጭ ኮሚቴው የድምፅ አሰጣጡን በብቃት ለመቆጣጠር እንዲቻል በክፍል 5 መሰረት የተመዘገቡ በመልካም የአባልነት አቋም ላይ ያሉ አባላትን ዝርዝር ከሥራ አስፈጻሚው አካል የምስጢራዊነት ስምምነት በመፈረም ይወስዳል፡፡

19.5. ኮሚቴው ቅንና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የተቻለውን ያህል የበርካታ አባላትን አስተያየት ያሰባስባል፡፡

19.6. ኮሚቴው የእጩዎችን ዝርዝር የሚያዘጋጀዉ፣ በክፍል 5 መሰረት በተመዘገቡ በመልካም የአባልነት አቋም ላይ ካሉ ከማንኛዉም አባላት፣ ጥቆማዎችን በመቀበል ይሆናል።

19.7. ለቦርድ አባልነት፣ ለምርጫ ከሚፈለገዉ ቁጥር በላይ፣ ቢያንስ በሁለት ቁጥር የበለጡ እጩዎች ይዘጋጃሉ። የተጠቆሙት ሰዎች ክፍት ከሆነው ቦታ ቁጥር ከሁለት በታች ከሆኑ እጩዎች በአጠቃላይ ስብሰባውም ወቅት ከሙሉ አባላት ሊጠቆሙ ይችላሉ፡፡

19.8. ኮሚቴው የእጩዎችን ዝርዝር ሲያዘጋጅ ለማኅበሩ ዓላማዎች ያላቸውን ቁርጠኝነት፣ ግልጋሎት ለመስጠት ዝግጁነትና ያላቸውን ተፈላጊ እውቀትና ችሎታ ከግምት ውስጥ ያስገባል።

19.9. ኮሚቴው ያዘጋጀው የእጩዎች ዝርዝር ለማኅበሩ አባላት ይሰራጭ ዘንድ ቢያንስ ከሦስት ሳምንታት ቀደም ብሎ ለቦርዱ ያቀርባል፡፡

19.10.  የምርጫ ኮሚቴው የሥራ ተግባሩን የሚያጠናቅቀው ምርጫው እንደተካሄደ ይሆናል፡፡

19.11.  የአስመራጭ ኮሚቴው ሥራዉን ካጠናቀቀ በኋላ ለምርጫ የተጠቀመባችዉን ሰነዶች ለቦርዱ ማስረከብ ይኖርበታል። የዲጂታል መዝገቦችንም መደምሰስ ይኖርበታል።

 

ክፍል 20

ድምፅ አሰጣጥ

 

20.1. የምርጫ ኮሚቴው ሰብሳቢ በጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ወቅት የእጩዎችን ስም ዝርዝር በድጋሜ ለአባላት ያቀርባል።

20.2. በክፍል 5 መሰረት የተመዘገቡና በመልካም የአባልነት አቋም ላይ ያሉ ሙሉ አባላት በእያንዳንዱ እጩ ላይ ድምፅ በመስጠት ከፍተኛውን ድምፅ ያገኙ እጩዎች ለቦርድ አባልነት አሸናፊ ሆነው ይመረጣሉ፡፡

20.3. አንድ የማኅበሩ ሙሉ አባል አንድ ድምፅ ብቻ ይኖረዋል፡፡

20.4. ማንኛውም ከአባልነቱ ያልለቀቀ/ያልታገደ ወይም ከአባልነት ያልተሰረዘ በመልካም የአባልነት አቋም ላይ ያለ ሙሉ አባል በማናቸውም በማኅበሩ ስብሰባ ወቅት ድምፅ የመስጠት መብት ይኖረዋል፡፡ ድምፅ አሰጣጥ በራሳቸው በድምፅ ሰጪዎች ወይም በወኪሎቻቸው አማካኝነት በምስጢር ይካሄዳል፡፡

20.5. በምርጫ ላይ መገኘት ያልቻለ አንድ ሙሉ አባል የምርጫ ውክልና ሥልጣን በጽሑፍ በማሀበሩ ጽ/ቤት በኩል ወይም በቀጥታ ለአስማራጭ ኮሚቴዉ መስጠት ይችላል ።

 

ምእራፍ ስምንት ክፍያ እና የበጀት ዓመት ክፍል 21

21.1. ማንኛውም የቦርድ፣ የአባሪ ሥራ አስፈጻሚ፣ የንዑሳን ኮሚቴዎች እና የአማካሪ ኮሚቴ አባል በማኅበሩ ለሚያበረክተው አገልግሎት በጥሬ ገንዘብም ሆነ በዓይነት ክፍያ አያገኝም፡፡ ሆኖም አባሉ ለማኅበሩ ሥራ ከግሉ ያወጣው የገንዘብ ወጪ ሲኖር በማህበሩ ስራ አመራር ተጣርቶ፣ ተመላሽ ይደረግለታል፡፡

21.2. የማኅበሩ የበጀት ዓመት እ.ኤ.አ. ከመጋቢት (March) 1 እስከ የካቲት (February) 28 ይሆናል።

 

ምእራፍ ዘጠኝ

ሥልጣን

 

ክፍል 22

ማኅበሩ ዓላማዎቹን ያሳካ ዘንድ፡-

 

22.1. ቋሚ ንብረት ሊገዛ እና ሊሸጥ፣ሊያከራይ ወይም ለሌላ ወገን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡

22.2. ማኅበሩ የንብረቶቹ፤ የገንዘቡና የሀብቱ ባለቤት ሲሆን፣ ይህንንም የሚያስተዳድረው የአልበርታ ክፍለ ግዛት የማኅበራት ሕግን፣ በዚህ ሕገ ማኅበርና በመተዳደሪያ ደንቡ የጸደቁትን የሥራ አመራር ፖሊሲዎች እንዲሁም በጠቅላላ ስብሰባዎች ቀርበው በአባላት የጸደቁ ውሳኔዎችን በጥብቅ በማክበር ይሆናል፡፡

22.3. የማኅበሩ  ንብረቶች  የሚመዘገቡት  በካልጋሪ  የኢትዮጵያ  ማኅበረሰብ  ማኅበር  ስም  ሲሆን፣  ማኅበሩ ለተቋቋመባቸው ዓላማዎች ብቻ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

22.4. ማኅበሩ ይህንን ሕገ ማኅበር እና መተዳደሪያ ደንቡን በሚያከብርና ለማኅበሩ ዓላማዎች ግንዛቤ በሰጠ መንገድ የገንዘብ ማሰባሰብ ሊያካሂድ፣ ገንዘብ ሊበደር እና ክፍያዎችን ሊፈጽም ይችላል፡፡ የማህበሩ የስራ አመራር፣ አካል ለማህበሩ አግልግሎት ገንዘብ ለመበደር ይረዳ ዘንድ፣ ይህን ህገ ማህበርና የመተዳደሪያ ደንቡን በተከተለ ሁኔታ፣ የብድር መመሪያ (Borrowing Bylaw) በማዘጋጀት፣ ለቦርዱ አቅርቦ ያጸድቃል።

22.5. ማኅበሩ በሥራ አመራሩ ወይም በቦርዱ አማካኝነት፣ ከሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ጋር ሕጋዊ ስምምነቶችን ሊፈጽም ይችላል፡፡

 

ምእራፍ አስር

ስለ ኦዲት (የሂሳብና የንብረት ምርመራ)

 

ክፍል 23

23.1. ማህበሩ ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤ የሆነ የኦዲት ኮሚቴ ይኖረዋል።

23.2. የኦዲት ኮሚቴ አባላት በቦርዱ ታጭተው በጠቅላላው ጉባኤ ይፀድቃሉ።

23.3. የአስተዳደርና የፋይናነስ ሙያና ልምድ ያለው ማንኛዉም አባል እንዲሁም አባል ያልሆነ ግለሰብ  ለኦዲት ኮሚቴ አባልነት ዕጩ መሆን ይችላል።

23.4. የኦዲት ኮሚቴው ሶስት አባላት ይኖሩታል የስራ ዘመናቸዉም ሶስት ዓመት ይሆናል።

23.5. ኮሚቴው ከመካከላቸው ሰብሳቢና ፀሃፊ ይመርጣሉ።

23.6. የጥቅም ግጭትን ለማስወገድና ፍፁም ገለልተኘነትን ለማስከበር የዚህ ኮሚቴ አባላት በማንኛዉም የማህበሩ ኮሚቴ ዉስጥ ተመርጠዉም ሆነ በፈቃደኝነት ማገልገል አይችሉም። አንዲሁም በስራም ሆነ በጥቅም ከቦርድ አባላት ጋር ግኑኝነት አንዲኖራቸው አያስፈልግም።

23.7. ቢያንስ አንዱ የኮሚቴዉ አባል በዘመናዊ ሂሳብ የስራ ልምድ ያለው መሆን አለበት።

23.8. ኮሚቴው በየስድስት ወር የማህበሩን ንብረት፣ ሂሳብ፣ የፅህፈት ቤቱን መዝገብና ጠቅላላ አሰራር ይመረምራል፣ ይቆጣጠራል። መስተካከልና መታረም የሚገባቸውን ጉዳዮች ከማሻሻያ ሐሳብ ጋር ለቦርዱ ያቀርባል።

23.9. ቦርዱ ለጠቅላላ ጉባኤዉ የሚያቀርበው አመታዊ  የሂሳብ  ሪፖርት  በኦዲት ኮሚቴው የተመረመረ  መሆን ይኖርበታል።

23.10.  የኦዲት ኮሚቴው በአመቱ ዉስጥ አጣርቶ ያገኘዉን ዉጤትና ለተከሰቱት ስህተቶችና ችግሮች መፍትሄ ሃሳቦችን ያካተተ ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባኤው አመታዊው ስብሰባ ላይ ማቅረብ ይኖርበታል።

23.11.  በቦርድ አባላት መካከል አለመግባባት ከተፈጠረና የማህበሩን እድገት እንቅፋት መሆን ሲጀምር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ እንዲጠራ ቦርዱን በፅሁፍ ይጠይቃል።

23.12.  ኦዲት ኮሚቴው የማህበሩን ሰነዶች በማንኛዉም ጊዜ የማግኘት መብት አለው፤ ሆኖም ግን በማንኛዉም መንገድ የማህበሩን ሰነዶች ከማህበሩ ፅህፈት ቤት ይዞ መዉጣት አይፈቀድም።

23.13.  የቦርድ አባላት ለኦዲት ኮሚቴ እጩ መሆን የሚችሉት የስራ ዘመናቸዉን ከጨረሱ ከሁለት አመት በኋላ ይሆናል።

 

ምእራፍ አሥራ አንድ

ከለላ ስለመስጠት

ክፍል 24

 

24.1. ማህበሩ ለማኅበሩ ዓላማ ተፈጻሚነት በታማኝነት ኃላፊነት በመውሰድ በአስተዳደርና በማኅበራዊ ሁኔታዎች ግዴታውን ለተወጣ በሥራ ላይ ላለ ወይም ለነበረ ማንኛዉም አባል ለሚደርስበት ክስ እና ዉንጀላ ተገቢዉን ከለላ ያደርጋል። ከዚህም የተነሳ ለሚደርሰዉ ማንኝዉም ጉዳት ተገቢዉን ካሳ ይከፍላል።

ምእራፍ አስራ ሁለት የማኅበሩ መፍረስ ክፍል 25

25.1. ማኅበሩ በአልበርታ ክፍለ ግዛት ማህበረሰብ መመሪያ (ሶሳይቲ አክት) ሕግ መሠረት ሊፈርስ ይችላል፡፡ ማኅበሩ ሊፈርስ የሚችለው ቦርዱ በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ለአባላት የሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ ሲጸድቅ ብቻ ይሆናል።

25.2. ቦርዱ ማኅበሩን ስለማፍረስ የውሳኔ ሐሳብ ለጠቅላላ ጉባኤው ከማቅረቡ ቢያንስ ከ30 ቀናት በፊት ለአባላት የጽሑፍ ማስታወሻ ማህበሩ በሚጠቀምባቸዉ የመገናኛ ዘዴዎች  መላክ ይኖርበታል፡፡

25.3. ማኅበሩን የማፍረስ ፍላጎትንና የውሳኔ ሐሳብ የያዘ ጽሑፍ አባላት መጨረሻ በነበራቸው አድራሻ (የመኖሪያ ወይም ኢሜይል) እንዲሁም ማህበሩ በሚጠቀምባቸዉ የመገናኛ ዘዴዎች የሚላክ ሲሆን ከተላከ በአምስት ቀን በኋላ አባሉ እንደደረሰው ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

25.4. ማኅበሩን ለማፍረስ የሚቀርብ የውሳኔ ሐሳብ ለመጽደቅ በጠቅላላው ጉባኤ ከተገኙ አባላት የ95 ከመቶውን ድምጽ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

25.5. የማኅበሩ መፍረስ ከተጠናቀቀና ዕዳዎች በሙሉ ከተከፈሉ በኋላ የሚቀረው ንብረት ካናዳ ውስጥ ለተመሳሳይ ዓላማ ለተቋቋሙ ለትርፍ ላልቆሙ የኢትዮጵያውያን ማኅበራት ይከፋፈላል፡፡

25.6. ቦርዱ የፈረሰው ማኅበር ንብረት ሊሰጣቸው ይገባል የሚላቸውን ማኅበራት በመለየት ለአባላት ያሳውቃል፡፡

 

ምእራፍ አስራ ሶስት

የሕገ ማኅበርና የመተዳደርያ ደንብ መሻሻል

ክፍል 26

 

26.1. ይህ ሕገ ማኅበርና ተ ያ ያ ዥ የመተዳደርያ ደንብ አግባብ ባላቸው የአልበርታ ከፍለግዛት ገዢ ህጎች ላይ በሚደረግ ማሻሻያ/ለውጥ ላይ ተመርኩዞ ወይንም አባላት ሕገ ማኅበሩ ወይም መተዳደሪያ ደንቡ እንዲሻሻል ጥያቄ ሲያቀርቡ ወይንም ከቦርዱ የመነጨ የማሻሻያ ሃሳብ ሲኖር ቦርዱ በሚሰይማቸው ገለልተኛ የማኅበሩ አባላት ወይም ከላይ በክፍል 12 በተጠቀሰው የአማካሪዎች ምክርቤት አማካኝነት የማሻሻያ/ተለዋጭ ሕገ ማኅበር/መተዳደርሪያ ደንብ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለዚሁ ዓላማ በተጠራ የአባላት ዓመታዊ/ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ ሊሻሻል/ሊለወጥ ይችላል፡፡

26.2. አባላት በግል ወይም በቡድን ሕገ ማኅበሩን የማሻሻያ ረቂቅ ካዘጋጁ ያላቸውን ሐሳብ ለማኅበሩ ጸሐፊ/

ለፕሬዚዳንቱ ተከታዩ የሥራ አስፈጻሚው አካል ስብሰባ ከመደረጉ 60 ቀናት በፊት ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

26.3. በሕገ ማኅበሩና በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ ያልተካተቱ ተገቢ የፖሊሲና የአሠራር ልምዶች ተፈጻሚነት የሚኖራቸው ለማኅበሩ ጥቅም የሚሰጡ ከዚህ ሕገ ማኅበርና የመተዳደርያ ደንቡ ጋር የማይጋጩና በቦርዱ ድጋፍ ሲያገኙ ብቻ ይሆናል፡፡

26.4. ይህ ሕገ ማኅበር እና የመተዳደርያ ደንቡ ማኅበሩ የሚመራባቸው መሠረታዊ ሠነዶች ናቸው፡፡

 

ምእራፍ አስራ አራት

በሕገ ማኅበሩ እና በመተዳደርያ ደንቡ መካከል ያለ ግንኙነት

ክፍል 27

 

27.1. ማኅበሩ ከዚህ ሕገ ማኅበር ጋር የተያያዘ የመተዳደርያ ደንብ ይኖረዋል።

27.2. የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ከሕገ ማኅበሩ ጋር እኩል አቅም እና ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

27.3. ማንኛዉም የማኅበሩ አባልና ማህበሩን ለማገልገል የሚንቀሳቅሱ አባል ያልሆኑ ግለሰቦች  ይህንን ሕገ ማኅበር እና የመተዳደርያ ደንቡን ማክበር ይጠበቅባቸዋል።

27.4. ይህ ሕገ ማኅበርና በጠቅላላው ጉባኤ በመጽደቅ ከ…………………… ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለ የማኅበሩ ዋና የመተዳደርያ ሠነድ ሆኗል፡፡ ይህ ሕገ ማኅበር ከዚህ በፊት ሥራ ላይ የነበሩትን ሕግጋተ ማኅበር ይተካል፡፡

ካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ 
ማኅበር

ሕገ ማኅበር

​ምእራፍ አንድ

ስም እና ዓላማዎች

ክፍል 1

1. የማኅበሩ ስም ‹‹ካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህ ሠነድ ‹‹የካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር ሕገ ማኅበር 2010›› በመባል ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. የካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖት እና ከጎሣ ነጻ የሆነ ድርጅት ነው፡፡

3. የማኅበሩ ዓላማ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ያካትታል፡-

3.1. በካልጋሪ እና በካባቢው ነዋሪ የሆኑ የኢትዮጵያውያንን በሙሉ የጋራ ደህንነት እና ጥቅሞች ለማስጠበቅ መስራት፣

3.2. በሕዝብ መድረኮች እና በማኅበረሰብ የልማት መርሐ ግብሮች የአባላቱን የጋራ ጥቅሞች መወከል እና ማጎልበት፣ እና

3.3. የኢትዮጵያን ባሕል እና ማኅበራዊ እሴቶች ግንዛቤ በካናዳ ኅብረተሰብ ዘንድ በሠፊው ማዳበር፣

 

ምዕራፍ ሁለት

ትርጓሜ፣ ማሕተም እና ቋንቋ

ክፍል 2

ትርጓሜ

1. በዚህ ሕገ ማኅበር፣ መተዳደሪያ ደንብ እና በሌሎች ተያያዥ የማኅበሩ ሠነዶች፣ ‹‹ማኅበሩ›› ማለት ‹‹ካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር›› ማለት ነው፣

2. ‹‹መተዳደርያ ደንብ›› በዚህ ሠነድ ስለ እያንዳንዱ ክፍል አግባብነት ያላቸውን ዝርዝር ድንጋጌዎች የያዙ እና የዚህ ሕገ ማኅበር ደጋፊ ተደርገው የሚወሰዱት ናቸው፡፡

3. በዚህ ሕገ ማኅበር፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን›› ማለት በምሥራቅ አፍሪካ ከምትገኘው ኢትዮጵያ የመጡ ወይም ከእነርሱ የተወለዱ፣ በአሁኑ ወቅት በካልጋሪ እና በአካባቢው በቋሚነት ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ማለት ነው፣

4. ‹‹አባል›› ማለት በዚህ ሕገ ማኅበር በክፍል 5(4) በተጻፈው መሠረት በመልካም የአባልነት አቋም ላይ የሚገኝ ማንኛውም አንድ ወይም ጠቅላላውን አባላት ማለት ይሆናል፡፡

5. ‹‹ተባባሪ አባል›› ማለት የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ ሕፃናትን በጉዲፈቻ የወሰደ እና እንደዚህ ያሉ ልጆች ከኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጋር ትስስር እንዲኖራቸው እና በካልጋሪ በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ልዩ ልዩ ተግባራት ውስጥ ለመሳተፍ የማኅበሩ አባል ለመሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ማለት ነው፡፡

6. ‹‹ሕግ›› ማለት በዚህ ሠነድ እንደተጠቀሰው የአልበርታ የማኅበራት ሕግ ማለት ሲሆን እንደዚህ ባለው ሕግ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚደረጉ ማሻሻያዎች በዚህ ትርጓሜ ሥር የሚካተቱ ይሆናሉ፣

7. ‹‹ዋነኛ ተነሳሽነት›› ማለት ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው የፋይናንስ እና/ወይም ከፋይናንስ ውጭ የሆኑ የግብዓት ግዴታዎች አንጻር ማኅበሩ ግዴታ ሊገባባቸው። የሚችልባቸው ጉዳዮች ማለት ይሆናል፡፡

8. ‹‹የጋራ ስብሰባ›› ማለት የቦርድ አባላት እና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በጋራ የሚያካሂዱት ስብሰባ ማለት ነው፡፡

ክፍል 3

የማኅበሩ ማሕተም

1. የማኅበሩ ማኅተም በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የማኅበሩ ስያሜ የሚቀረጽበት ሲሆን በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በጸደቀው አኳኋን ይዘጋጃል፡፡

2. የማኅበሩ ጸሐፊ የማኅበሩን ማሕተም በኃላፊነት ይይዛል፤ ማሕተሙ ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ ሁሉ የጸሐፊው እና የፕሬዚዳንቱ ፊርማ ወይም (እነዚህ የሥራ ኃላፊዎች ፊርማቸውን ማኖር በማይችሉበት ወቅት) ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ፊርማ ጋር አብሮ መስፈር ይኖርበታል፡፡

ክፍል 4

ቋንቋ እና አተረጓጎም

1. በዚህ ሕገ ማኅበር እንዲሁም ተያያዥነት ባላቸው የመተዳደሪያ ደንብ ሠነዶች በተባዕት ወይም በነጠላ የተገለጸ ቢኖር አንስታይ ወይም ብዙ ቁጥርን፣ በአንስታይ እና በብዙ ቁጥር የተገለጸ ደግሞ ተባእት እና ነጠላ ቁጥርን የሚያካትት ይሆናል፡፡

2. አማርኛ የማኅበሩ የሥራ ቋንቋ ሲሆን እንግሊዝኛ ቋንቋ ደግሞ ለውጭ ግንኙነት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ሆኖም ግን ማንኛውም የማኅበሩ አባል በማናቸውም በኢትዮጵያ ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች ከማኅበሩ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ቢፈልግ ማኅበሩ አባሉን ለማስተናገድ የተቻለውን ጥረት ሁሉ ያደርጋል፡፡

3. ማኅበሩ ከውጭ አካላት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት አግባብነት ያላቸውን ሠነዶቹ እንዲሁም የፋይናንስ መግለጫዎችንና ሬከርዶቹን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲተረጎሙ እና እንዲቀመጡ ያደርጋል፡፡

ምዕራፍ ሶስት

አባልነት

ክፍል 5

ብቁነት

1. አመልካቾች ለአባልነት ብቁ ለመሆን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ማሟላት ይኖርባቸዋል፡-

1.1 እድሜያቸው ቢያንስ 18 ዓመት የሆነና በካናዳ ቋሚ ነዋሪ የሆኑ ወይም በካናዳ ቢያንስ ለ3 ወራት በሕጋዊ ነዋሪነት የቆዩ መሆን አለባቸው፤

1.2 በካልጋሪ ከተማ እና/ወይም በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወይም የእነርሱ ተወላጆች መሆን አለባቸው፤

1.3 የማኅበሩን ዓላማዎች እና ተልዕኮ ለመደገፍ ጊዜያቸውን እና ጥረታቸውን በበጎ ፈቃደኝነት ለማበርከት የሚስማሙ መሆን አለባቸው፣

2. አንድ አመልካች ተባባሪ አባል ለመሆን በክፍል አምስት (1.1) መሠረት አባል ለመሆን የማይችሉ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ልጆች/ ጉዲፈቻ ልጆች ወላጅ መሆን ይኖርበታል፤

3. ‹‹ተባባሪ አባላት›› የመምረጥ ወይም በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባል ለመሆን ወይም በቦርድ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ መወዳደር አይችሉም፡፡ ነገር ግን ተባባሪ አባላት በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ሥር ላሉ ንUሳን ኮሚቴዎች ሊመረጡ ይችላሉ፡፡

4. ለአባልነት ብቁ የሆነ ማናቸውም ሰው በዚህ ሕገ ማኅበር መሠረት በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የተዘጋጀውን ቅጽ በመሙላት ለአባልነት ማመልከት ይኖርበታል፡፡

5. እያንዳንዱ አባል በጠቅላላ ጉባኤው በተወሰነው መሠረት የምዝገባ እና የአባልነት ክፍያዎችን ለማኅበሩ ገንዘብ ያዥ መክፈል ይኖርበታል፡፡

6. ማንኛውም የማኅበሩ አባል የአባልነት ክፍያዎችን በወቅቱ መክፈል እና በማኅበሩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል፡፡

ክፍል 6

እግድ፣ ከአባልነት መሰናበት እና አባልነትን መልሶ

ስለማግኘት

1. ማንኛውም አባል ከማኅበሩ አባልነት መልቀቅ ሲፈልግ ፍላጎቱን በጽሑፍ በማሳወቅ ከአባልነት መሰናበት ይችላል፡፡

2. ማንኛውም አባል ለስድስት ተከታታይ ወራት የአባልነት ክፍያውን ካልከፈለ ከአባልነት ታግዶ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ አባሉ ወደ አባልነት አቋሙ እስኪመለስ ድረስ ማናቸውም የአባልነት መብት/ሥልጣን አይኖረውም፡፡

3. የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ልዩ ስብሰባ አንድን አባል ከሦስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ከማኅበሩ ሊያግድ ይችላል፡፡ ይህ ተፈጻሚ የሚሆነው ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አንድ/ከዚያ በላይ በሆኑ ምክንያቶች እና ከኮሚቴው አባላት መካከል 75 ከመቶ በሆኑት ሲደገፍ ይሆናል፤

3.1 ሕገ ማኅበሩን አለማክበር፤

3.2 የማኅበሩን ስብሰባ፤ እንቅስቃሴና አገልግሎት ማወክ፤

3.3 ለማኅበሩ ጎጂ በሆነ ድርጊት ውስጥ ተሣታፊ ሆኖ ከተገኘ፤

4. ቦርዱ በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በሚቀርብለት የውሳኔ ሐሳብ መሠረት አንድን አባል ከሦስት ወራት ለበለጠ ጊዜ (ጠቅላላ ስብሰባ እስኪካሄድ) ከአባልነት ሊያግድ ይችላል፡፡

5. ማንኛውም አባል የማኅበሩ ጠቅላላ ስብሰባ አግባብ ነው ብሎ ባመነበት ማናቸውም ምክንያት እና በ2/3ኛ አብላጫ ድምጽ ከአባልነቱ ሊሰረዝ ይችላል፡፡

6. በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ከአባልነት የተሰረዙ አባላት በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት ስብሰባዎችን የመከታተል እና የመወከል መብት አላቸው፡፡

7. ማንኛውም ከአባልነት የተሰረዘ አባል ከስድስት ወራት በኋላ የአባልነት ማመልከቻ በድጋሚ ማቅረብ ይችላል፡፡ የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ጉዳዮን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል፡፡

ምዕራፍ አራት

ድርጅታዊ መዋቅር

ክፍል 7

ማኅበሩ የሚከተሉት አካላት ይኖሩታል፤

ሀ. ጠቅላላ ጉባኤ፣

ለ. ቦርድ፣

ሐ. ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣

መ. የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ንዑሳን ኮሚቴዎች፤

 

ክፍል 8

ጠቅላላ ጉባኤ

1. ጠቅላላ ጉባኤው የማኅበሩ ከፍተኛ ፖሊሲ አውጪ እና ውሳኔ ሰጪ አካል ነው፡፡

ክፍል 9

ቦርድ

1. ቦርዱ የማኅበሩን አጠቃላይ ደህንነትና የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴን በበላይነት የሚቆጣጠሩ አምስት ተመራጭ አባላትን ያካትታል፡፡

2. የቦርዱ አባላት ለሦስት ዓመት የአገልግሎት ዘመን በጠቅላላ ጉባኤው ይመረጣሉ፡፡ ቦርዱ ከአባላቱ መካከል አንድ ሊቀመንበር ይመርጣል፡፡

3. ቦርዱ የማኅበሩን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ በተመለከተ ኃላፊነት ባይኖርበትም በዚህ ሕገ ማኅበር በክፍል 14 መሠረት የተወሰኑ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ጋር በጋራ ውሳኔ የመስጠት ድርሻ ይኖረዋል፡፡

4. ቦርዱ የማኅበሩን ዓመታዊ በጀት እና የሥራ እቅድ የማጽደቅ ሥልጣን አለው፡፡ ከዚህም ሌላ ቦርዱ በጸደቀው በጀት/የሥራ እቅድ በግልጽ ያልተቀመጡ ሌሎች ዋና የሥራ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም በማኅበሩ ዓላማዎች እና የወደፊት አቅጣጫ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ይኖረዋል፡፡

5. ቦርዱ ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ጋር በዋና የፖሊሲ እና የውሳኔ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ከተፈጠረ ጉዳዩ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ለቀጣዩ መደበኛ/ልዩ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ሊያቀርብ ይችላል፡፡

6. ቦርዱ በማናቸውም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወይም በሌላ ማንኛውም አባል ላይ የቀረበን አቤቱታ ሊመረምር የሚችል ሲሆን አስፈላጊ ከሆነ ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ በመጨመር ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል፡፡

7. ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት መካከል የ75 ከመቶ ድጋፍ መሠረት ቦርዱ የአንድ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልን እግድ እስከ ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ሊያጸድቅ ይችላል፡፡

8. ቦርዱ ከአባላቱ መካከል የ75 ከመቶ ድጋፍ ካገኘ አንድን የቦርድ አባል በሕገ ማኅበሩ መሠረት ግዴታዎችን ባለመወጣት/ ሕገ ማኅበሩን በመጣስ እስከሚቀጥለው ጠቅላላ ስብሰባ ድረስ ሊያግድ ይችላል።

9. ቦርዱ በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አንድ አባል/በራሱ አባላት ላይ የቀረበን አግባብነት ያለው ማናቸውንም አቤቱታ ሊመረምር እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከውሳኔ ሐሳብ ጋር የምርመራውን ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባዔ ሊያቀርብ ይችላል፡፡

10. አራት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ማለትም ፕሬዚዳንቱ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ጸሐፊው፣ ገንዘብ ያዡ እና የፋይናንስ ኃላፊው (የማሕበራዊ ጉዳዮች እና የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰሩን ሳይጨምር) በገዛ ፈቃዳቸው ሲለቁ ወይም ከኃላፊነታቸው ሲነሱ ቦርዱ የሚከተለውን ይፈጽማል።

10.1. ክፍት የኃላፊነት ቦታዎች በልዩ ጠቅላላ ስብሰባ በተቻለ ፍጥነት እስኪሟሉ ድረስ አስተዳደሩንና የንብረት ቁጥጥርን በኃላፊነትን ይመራል፡፡

10.2. ክፍት ለሆኑ የኃላፊነት ቦታዎችን ከአባላቱ መካከል በጊዜያዊነት ይመድባል፡፡

10.3. በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ይሰሩ ለነበሩ አባላት የሥራ መልቀቂያ ማስረጃ በይፋ ከመስጠቱ በፊት/ወዲያውኑ የኦዲት ማጣራት እንዲካሄድ ያደርጋል፡፡

10.4. ከማኅበሩ ከኃላፊነት ቦታ የተነሱ አባላት ያላቸውን በቼክ እና በባንክ ሠነዶች ላይ የመፈረም ሥልጣን ይሰርዛል፣ ለሚመለከታቸው ባንኮች ወዲያውኑ ያሳውቃል፡፡

10.5. የመፈረም ሥልጣን የማኅበሩን የእለት ተዕለት ሥራዎች ለማካሄድ ያህል ብቻ (በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት) ተፈጻሚ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

11. ማናቸውም የቦርድ አባል ከሁለት ተከታታይ ጊዜ በላይ ሊመረጥ አይችልም፡፡

12. በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት በሚሰጥ አብላጫ ድምጽ መሠረት ማንኛውም አባል ማኅበሩ ተገቢ ሆኖ ባገኘው ምክንያት ከኃላፊነቱ ሊነሳ ይችላል፡፡

13. ሁለት ተከታታይ የኃላፊነት ጊዜያትን ያጠናቀቀ የቦርድ አባል ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል ለሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባልነት መወዳደር አይችልም፡፡

ክፍል 10

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

1. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የማኅበሩን እንቅስቃሴ እና ጉዳዮችን የሚመራና የሚያካሂድ አካል ሲሆን፣ በዚህ ሕገ ማኅበር፣ በመተዳደርያ ደንቡ እና በሌሎች ተያያዥነት ባላቸው ሠነዶች እና አሠራር መሠረት ማኅበሩን በመወከል እና በማኅበሩ ስም የማኅበሩን ሥልጣን ይጠቀማል፡፡

2. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ሰባት አባላት ይኖሩታል፡፡ እነዚህም አባላት በአልበርታ የማኅበራት ሕግ መሠረት አግባብነት ባለው ሬጂስትራር ዘንድ ተመዝግበው በመተዳደርያ ደንቡ በተሰጣቸው ኃላፊነትና የሥራ ድርሻ ዝርዝር መሠረት ተግባራቸውን ያከናውናሉ፡፡

በኮሚቴው ውስጥ የሚከተሉት አባላት ይካተታሉ፡-

ሀ. ፕሬዚዳንት

ለ. ምክትል ፕሬዚዳንት

ሐ. ጸሐፊ

መ. ገንዘብ ያዥ

ሠ. የፋይናንስ ኦፊሰር

ረ. የማሕበራዊ ጉዳዮች ኦፊሰር

ሰ. የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር

3. የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት በዚህ ሕገ ማኅበሩ እና በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት ለሁለት ዓመታት ጊዜ በጠቅላላ ጉባኤው ይመረጣሉ፡፡ ማንኛውም የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባል ከሁለት ተከታታይ ጊዜያት በላይ ሊመረጥ አይችልም፡፡

4. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የማኅበሩ ንብረቶች ያዥ ከመሆኑም በላይ እነዚህን የመቆጣጠር እና የመምራት ኃላፊነት አለበት፡፡ እነዚህንም ንብረቶች በአልበርታ ክፍለ ግዛት ሕግጋት፣ በካልጋሪ ከተማ መተዳደሪያ ሕግ እንዲሁም ከበላይ አስተዳደር አካላት በየጊዜው በሚወጡ የሥራ አመራር ፖሊሲዎች እና አሠራር መሠረት የማስተዳደር ግዴታ ይኖርበታል፡፡

5. የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ዓመታዊ በጀትንና ዋና የሥራ እቅድን ያዘጋጃል፡፡ የማኅበሩን ተለዋዋጭ ድርጅታዊ የሥራ ፍላጎትን በመለየት የፖሊሲ አፈጻጸምን ያዳብራል፣ ያዘጋጃል፡፡

6. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ተገቢ የሥራ አመራርና የማህደር አያያዝ ፖሊሲና አፈጻጸም በመቅረጽ ሥራ ላይ የማዋል ኃላፊነት አለበት፡፡

7. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በክፍል 11 መሠረት ንኡሳን ኮሚቴዎችን ያዋቅራል፣ አባላትንም ይመድባል፡፡

8. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ቋሚ እና ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን በማቋቋም የሥራ መመሪያ ይሰጣል፡፡

9. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የንዑሳን ኮሚቴዎችንና ቡድኖችን የተግባር እንቅስቃሴ በመከታተል እንደአስፈላጊነቱ አመራርና ድጋፍ ይሰጣል፡፡

10. በዋና የፖሊሲ እና/ወይም በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ ከቦርዱ ጋር ልዩነት ሲያጋጥም ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ጉዳዩን ለሚቀጥለው መደበኛ/ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ ለውሳኔ ያቀርባል፡፡

11. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ከዐባላቱ መካከል 75 ከመቶ ድጋፍ ሲያገኝ ግዴታን ባለመወጣት/ ይህንን ሕገ ማኅበር እና/ወይም መተዳደርያ ደንቡን የጣሰ አባል እንዲታገድ ለቦርዱ የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል፡፡

12. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ እና ከቦርድ አባላት ሌላ በማናቸውም አባል ላይ የቀረበን አቤቱታ ሊመረምር እና ሪፖርቱን እንደአስፈላጊነቱ ከውሳኔ ሐሳብ ጋር ለጠቅላላ ጉባዔ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በቀረበው አቤቱታ ዓይነት ላይ በመመስረት ለምርመራው ድጋፍ የሚሰጡ አባላት የተካተቱበት ቡድን ሊሰይም ይችላል፡፡

13. ማንኛውም የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባል በጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ማኅበሩ ባመነበት ምክንያትና በሚሰጥ አብላጫ ድምጽ ከኃላፊነት ሊነሣ ይችላል፡፡

ክፍል 11

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ንዑሳን ኮሚቴዎች

1. ማኅበሩ በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የሚመረጡ እና ለኮሚቴው ተጠሪ የሆኑ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ንዑሳን ኮሚቴዎች ሊኖሩት ይችላሉ፡-

 

ሀ. የሴቶች ኮሚቴ

ለ. የሕጻናት እና ወጣቶች ኮሚቴ

ሐ. የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚቴ

መ. የክበብ እና መዝናኛ ኮሚቴ

ሠ. የግንኙነት እና ሥልጠና ኮሚቴ

ረ. የባሕል እና ስፖርት ኮሚቴ

ሰ. የንብረት ጥበቃ እና ደህንነት ኮሚቴ

ሸ. የመርሐ ግብር ኮሚቴ

2. እያንዳንዱ ኮሚቴ በመተዳደሪያ ደንቡ በተዘረዘረውና ከሥራው ጋር አግባብነት ካለው ዓላማ፣ ተግባርና ኃላፊነት አኳያ ሥራውን ያከናውናል፡፡

ክፍል 12

የአማካሪዎች ምክር ቤት

1. አስተዳደራዊ ሥልጣን የማይኖረውና በጋራ ስብሰባ የሚመረጥ የአማካሪዎች ምክር ቤት ይቋቋማል፡፡

2. የምክር ቤቱ ተግባር ከዚህ በታች በተዘረዘረው መልክ ለማኅበሩ አመራር ምክር መለገስ ይሆናል፡-

2.1 ከማኅበሩ የሥራ አመራር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በቦርዱ እና/ወይም በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በሚሰጥ መመሪያ መሠረት በጋራ ወይም በተናጠል ምክር እና የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት፣

2.2 በጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ወቅት ቀርበው ውሳኔ የተሰጠባቸውን ጉዳዮች በመመዘን በተከታይ ጉባኤ ለአባላት የሚቀርቡ ሪፖርቶችን ማዘጋጀት፤ ሪፖርቶች ለጠቅላላ ጉባኤ ከቅረባቸው በፊት በቦርዱና በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡

2.3 በባሕላዊ እውቀትና እሴቶች፣አስተዳደር፣ የሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ ምክር እና መረጃ ይሰጣል፡፡

3. የምክር ቤቱ አባላት ቁጥርና ስብጥር ቦርዱና ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በየጊዜ ተገቢ ነው ብለው በሚወስኑት መሠረት ይሆናል፡፡

4. የአማካሪች ምክር ቤት አባል በአስተዳደር አካላት ቀርቦ በበቂ ምክንያት ካልተዋሰነ ወይም በራሱ ፍላጎት ከሃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ ካላቀረበ ባስተቅር ላልተወሰነ ጊዜ በአገልጎሎት ላይ ይቆያል።

ምዕራፍ አምስት

አመራር እና አናሰተዳደር

ክፍል 13

አሰተዳደር

1. ቦርዱ በማህበሩ የስራ አቋምና እንቅስቃሴ ላይ ውይይት ለማድረግ ቢያንስ በሦስት ወር አንድ ጊዜ መደበኛ ስብሰባ ያካሂዳል፡፡ አብላጫውን ቁጥር የያዙ የቦርድ አባላት በስብሰባው ከተገኙ መደበኛ ስብሰባ ይካሄዳል።

2. የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ በወር አንድ ጊዜ በኮሚቴው አብላጫ አባላት በሚወሰነው ቦታ፣ቀንና ጊዜ ይካሄዳል፡፡

3. ፕሬዚዳንቱ በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አብላጫው አባላት በዚህ ሕገ ማኅበር /መተዳደርያ ደንቡ መሠረት ጥያቄ ሲቀርብለት የኮሚቴውን ስቸኳይ ስብሰባ በማናቸውም ወቅት ሊጠራ ይችላል፡፡

4. አብላጫ ቁጥር ያላቸው የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት በማናቸውም የኮሚቴው ስብሰባ ላይ ከተገኙ ስብሰባውን ለማካሄድ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል፡፡ በስብሰባው የተገኙት የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት ምልዓተ ጉባዔውን የማያሟሉ ከሆነ የተገኙ አባላት በአብላጫ በሚሰጡት ውሳኔ የስብሰባውን ቀን ለሌላ ጊዜ በማራዘም በማስታወቂያ ይገልጻሉ፡፡

5. የኮሚቴው ስብሰባዎች በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ይካሄዳሉ፡፡

6. ማኅበሩ ኃላፊነታቸውንና ልዩ መብታቸውን አንዲሁም የማኅበሩን ንብረቶች ያለአግባብ በሚጠቀሙ አባላት ላይ የሥነ-ሥርዓት እና/ወይም ሕጋዊ እርምጃዎች የመውሰድ መብት አለው፡፡

ክፍል 14

የጋራ ስብሰባ

1. ቦርዱና የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት በጋራ ሊታዩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት የሚያካሂዱት የጋራ ስብሰባ ይኖራል፡፡ በኮሚቴዎቹ የጋራ ስብሰባ የሚወሰኑት ጉዳዮች የሚከተለውን ያካትታሉ፡-

1.1 ረቂቅ ዓመታዊ በጀትንና ዋና ዋና እቅዶችን የማጽደቅ ቅድመ ዝግጅት

1.2 የአማካሪዎች ምክር ቤት አባላት ምርጫ እና ሹመት

1.3 የምርጫ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እና ሹመት

1.4 ከቦርዱና ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በመወገድ/በገዛ ፈቃዳቸው በለቀቁ አባላት ምትክ ጊዜያዊ ኃላፊዎችን እስከ ተከታዩ የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ የመመደብ፤

1.5 ከማኅበሩ አባላት መካከል ኦዲተሮችን መሾም፤

1.6 ለማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርቡ ጊዜያዊና ዓመታዊ የኦዲት እና ሌሎች ሪፖርቶችን የመቀበል፤

2. በጋራ ስብሰባ የተሰጠ ውሳኔ የሚጸናው ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ (ከፕሬዚዳንቱ እና ከአራት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሌላ) ቢያንስ በሦስት የቦርድ አባላት ሲደገፍ ብቻ ይሆናል፡፡

3. የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ፕሬዚዳንት (የቦርዱ አባልም ነው) የጋራ ስብሰባዎችን ይጠራል፣ የሚካሄዱበትን ጊዜ ይወስናል፣ ስብሰባዎችን ይመራል፡፡

ክፍል አስራ አምስት

በገዛ ፈቃድ ኃላፊነትን መልቀቅ፣ ከኃላፊነት መነሳት እና ክፍት የኃላፊነት ቦታዎች

1. የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ወይም የቦርዱ አባል የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ በጽሑፍ በመስጠት በገዛ ፈቃዱ ኃላፊነቱን ሊለቅ ይችላል፡፡ ቀሪዎቹ የኮሚቴ አባላት ማስጠንቀቂያው በተሰጠበት ቀን ወዲያውኑ ወይም ተፈጻሚ ከሚሆንበት ቀን አንስቶ የኃላፊነት ቦታው ክፍት መሆኑን ያሳውቃሉ፡፡

2. አባላት ለዚሁ ዓላማ በተጠራ ልዩ የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ በሚሰጡት አብላጫ ድምጽ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት በማናቸውም ምክንያቶች አንድን የቦርድ ወይም የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባል ከኃላፊነት ሊያነሱ ይችላሉ፡-

2.1 ሕገ ማኅበሩ እና መተዳደሪያ ደንቡን አለማክበር፤

2.2 ማኅበሩን ሊጎዳ በሚችል ተግባር ላይ መገኘት፤ ወይም

2.3 የኃላፊነት ግዴታን አለመወጣት፤

3. ጠቅላላ ጉባኤው የቦርዱን ወይም የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባልን ማብራሪያ በመስማት ስለ አባሉ ከኃላፊነት መነሳት አስመልክቶ ውይይት በማድረግ ውሳኔ ይሰጣል፤

4. በዚህ መልኩ ውሳኔ የተላለፈባቸው የቦርድ/የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት ስብሰባዎችን የመከታተል እና የመወከል መብት ይኖራቸዋል፤

5. በቦርድ ወይም በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የኃላፊነት ቦታዎች በገዛ ፈቃድ በመልቀቅ/በመነሳት ክፍት ቦታ ሲኖር ቦርዱና ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ከሌሎች ኮሚቴዎች እጩዎችን በመፈለግ እስከ ተከታዩ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ እንዲያገለግሉ ይመድባሉ፡፡

ምዕራፍ ስድስት

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎች

ክፍል 16

ጠቅላላ ደንቦች

1. ማኅበሩ ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ እና ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ ይኖሩታል፡፡

2. የማኅበሩ ስብሰባዎች ለሕዝብ ክፍት ይሆናሉ፡፡ በስብሰባው የተገኙ አባላት አባል ያልሆኑ ሰዎች ስብሰባውን እንዳይሳተፉ ከፈለጉ በመደበኛ ውሳኔ በስብሰባው እንዳይገኙ ሊወስኑ ይችላሉ፡፡

3. ማናቸውም ስብሰባ በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በፕሬዚዳንቱ ወይም በምክትል ፕሬዚዳንቱ (ፕሬዚዳንቱ ከሌለ) ይመራል፡፡ ሁለቱም ኃላፊዎች በማይኖሩበት ሁኔታ ተሰብሳቢ አባላት ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት ውስጥ ሰብሳቢ ይመርጣሉ፡፡

4. የውሳኔ ሐሳብ በተለየ መልክ እንዲጸድቅ አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በስተቀር ድምጽ የሚሰጠው በስብሰባ በተገኙ አባላት አብላጫ ድምጽ ይሆናል፡፡

5. በማናቸውም ዓመታዊ ወይም ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ አብላጫ የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት እና 20 ከመቶ ከተሰብሳቢ አባላት ምልዓተ ጉባዔ ያሟላሉ፡፡

6. የማኅበሩ ጸሐፊ የስብሰባዎችን ትክክለኛ ቃለ ጉባዔ ይይዛል፡፡

7. ስብሰባዎች በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ይመራሉ፡፡

ክፍል 17

ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ

1. ማኅበሩ መደበኛ ጠቅላላ ስብሰባውን በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ የሚያካሂድ ሲሆን ለአባላት የስብሰባ ጥሪ በጽሑፍ ወይም በስልክ ይደረጋል፡፡

2. የጽሑፍ የስብሰባ ጥሪ በአባላቱ በመጨረሻ በሚታወቅ አድራሻ ስብሰባው ከሚካሄድበት ቢያንስ ከ 21 ቀናት ቀደም ብሎ ይላካል፡፡ ከስብሰባው ጥሪ ጋር የጠቅላላ መደበኛ ስብሰባው የአጀንዳ ግልባጭ ለአባላቱ ይላካል፡፡

3. በጽሑፍ Aማካኝነት የስብሰባ ጥሪውን ማስተላለፍ ካልተቻለ ጠቅላላ መደበኛ ስብሰባው ከሚካሄድበት ቀን ቢያንስ ከሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ በስልክ አማካኝነት ጥሪ ይደረጋል፡፡

ክፍል 18

ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ

1. ማኅበሩ የጠቅላላ አባላት ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው አስቸኳይ ጉዳዮችን ለማየት ልዩ ጠቅላላ ስብሰባዎችን ያካሂዳል፡፡

2. ልዩ ጠቅላላ ስብሰባው ከቦርድ አባላት ወይም ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት መካከል 2/3ኛ የሚሆኑት በጽሑፍ ሲጠይቁ በማንኛውም ወቅት ሊጠራ ይችላል፡፡

3. ከአባላቱ መካከል 25 ከመቶ የሚሆኑት በማንኛውም ወቅት በጽሑፍ ከጠየቁ ማኅበሩ ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፡፡

4. ለልዩ ጠቅላላ ስብሰባ የሚቀርብ የጽሑፍ ጥያቄ ስብሰባው የተጠራበትን ምክንያትና በስብሰባው ውይይት ሊደረግባቸው የታቀዱ ረቂቅ የውሳኔ ጉዳዮችን መጥቀስና ማካተት ይኖርበታል፡፡

5. የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ እንዲካሄድ ጥያቄ ሲቀርብለት አጀንዳ በማዘጋጀት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ስብሰባውን ይጠራል፡፡

6. ልዩ ጠቅላላ ስብሰባው ከሚካሄድበት ቢያንስ ከ14 ቀናት ቀደም ብሎ አጀንዳውን ያካተተ እና በጽሑፍ የተዘጋጀ የስብሰባ ጥሪ ለአባላት (ለመጨረሻ ጊዜ በሚታወቅ አድራሻ ) ይላካል፡፡

7. በልዩ ጠቅላላ ስብሰባው ለውይይት የሚቀርቡትና ውሳኔ የሚተላለፍባቸው ጉዳዮች በስብሰባ ጥሪው አጀንዳ የተካተቱት ብቻ ይሆናሉ፡፡

ምዕራፍ ሰባት

ምርጫ እና ድምጽ አሰጣጥ

ክፍል 19

የምርጫ ኮሚቴ

1. አምስት አባላት (ቢያንስ) ያሉት የምርጫ ኮሚቴ በጋራ ስብሰባ ይመረጣል፡፡ ኮሚቴው ከጠቅላላ አባላት መካከል ብቁ የሆኑና ጠቅላላ ጉባኤው ለኃላፊነት ቦታ ሊመርጣቸው ይገባል የሚላቸውን ሰዎች በመለየት ዝርዝር ያዘጋጃል፡፡

2. ኮሚቴው ምርጫውን ለማካሄድ የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ከሚካሄድበት ቀን ቢያንስ ከስድስት ሳምንት ቀደም ብሎ መመሥረትና ኃላፊነቱን መረከብ ይኖርበታል፡፡

3. ኮሚቴው ከአባላቱ መካከል ሰብሳቢ ይመርጣል፡፡

4. የምርጫ ኮሚቴው የድምጽ አሰጣጡን በብቃት ለመቆጣጠር እንዲቻል የአባላትን ዝርዝር ከሥራ Aስፈጻሚው ኮሚቴ ይወስዳል፡፡

5. ኮሚቴው ቅንና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የተቻለውን ያህል የበርካታ አባላትን፣ አስተያየት ያሰባስባል፡፡

6. ኮሚቴው የእጩዎችን ዝርዝር ሲያዘጋጅ ለማኅበሩ ዓላማዎች ያላቸውን ቁርጠኝነት፣ ግልጋሎት ለመስጠት ዝግጁነትና ለእያንዳንዱ የሥራ መደብ ያላቸውን ተፈላጊ እውቀትና ችሎታ ከግምት ውስጥ ያስገባል፡፡

7. ኮሚቴው ያዘጋጀው የእጩዎች ዝርዝር ለማኅበሩ አባላት ይሰራጭ ዘንድ ቢያንስ ከሦስት ሳምንታት ቀደም ብሎ ለጋራ ስብሰባው ያቀርባል፡፡

8. የምርጫ ኮሚቴው የሥራ ተግባሩን የሚያጠናቅቀው ምርጫው እንደተካሄደ ይሆናል፡፡

ክፍል 20

ድምጽ አሰጣጥ

1. የምርጫ ኮሚቴው ሰብሳቢ በጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ወቅት የዕጩዎችን ስም ዝርዝር ለአባላት ያቀርባል፡፡ እጩዎች በስብሰባውም ወቅት ከአባላት ሊመረጡ ይችላሉ፡፡

2. አባላት በእያንዳንዱ እጩ ላይ ድምጽ በመስጠት ከፍተኛውን ድምጽ ያገኙ እጩዎች በቀረቡበት የኃላፊነት ቦታ አሸናፊ ሆነው ይመረጣሉ፡፡

3. አንድ የማኅበሩ አባል አንድ ድምጽ ይኖረዋል፡፡

4. ማንኛውም ከአባልነቱ ያልለቀቀ/ያልታገደ ወይም ከአባልነት ያልተሰረዘ አባል በማናቸውም በማኅበሩ ስብሰባ ወቅት ድምጽ የመስጠት መብት ይኖረዋል፡፡ ድምጽ አሰጣጥ በራሳቸው በድምጽ ሰጪዎች ወይም በወኪሎቻቸው አማካኝነት በምስጢር ይካሄዳል፡፡

5. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የአጀንዳውን ይዘት በመመርመር በወኪል አማካይነት ድምጽ መስጠት የሚቻል ስለመሆኑ የውሳኔ ረቂቅ ለቦርዱ ያቀርባል፡፡

6. ለአንድ አባል የሚሰጥ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ በጽሑፍ የተዘጋጀ መሆን ይኖርበታል፡፡ የውክልና ማስረጃው የውክልና ሥልጣኑን የሚሰጠውና/የሚቀበለው አባላትን ስሞች መያዝ ይኖርበታል፡፡ የውክልና ሥልጣን ማስረጃ ለምርጫ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይም ለተጠሪው መቅረብ አለበት፡፡

ምዕራፍ ስምንት

ክፍያ እና የበጀት ዓመት

ክፍል 21

1. ማንኛውም የቦርድ፣ የሥራ አስፈጻሚው ወይም የንዑሳን ኮሚቴዎች አባል በማኅበሩ ለሚያበረክተው አገልግሎት በጥሬ ገንዘብም ሆነ በዓይነት ክፍያ አያገኝም፡፡ ሆኖም አባሉ ለማኅበሩ ሥራ ከግሉ ያወጣው ወጪ ሲኖር ተመላሽ ይደረግለታል፡፡

2. የማኅበሩ የበጀት ዓመት እ.ኤ.አ. ከሚያዚያ 1 እስከ መጋቢት 31 ይሆናል፡፡

ምዕራፍ ዘጠኝ

ሥልጣን

ክፍል 22

ማኅበሩ ዓላማዎቹን ያሳካ ዘንድ፡-

1. ቋሚ ንብረት ሊገዛ እና ሊሸጥ፣ ሊያከራይ ወይም ለሌላ ወገን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡

2. ማኅበሩ የንብረቶቹ፤ የገንዘቡና የሀብቱ ባለቤት ሲሆን፣ ይህንንም የሚያስተዳደረው የአልበርታ ክፍለ ግዛት የማኅበራት ሕግን፣ በዚህ ሕገ ማኅበርና በመተዳደሪያ ደንቡ የጸደቁትን የሥራ አመራር ፖሊሲዎች እንዲሁም በጠቅላላ ስብሰባዎች ቀርበው በአባላት የጸደቁ ውሳኔዎችን በጥብቅ በማክበር ይሆናል፡፡

3. የማኅበሩ ንብረቶች የሚመዘገቡት በካልጋሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር ስም ሲሆን፣ ማኅበሩ ለተቋቋመባቸው ዓላማዎች ብቻ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

4. ማኅበሩ ይህንን ሕገ ማኅበር እና መተዳደሪያ ደንቡን በሚያከብር እና ለማኅበሩ ዓላማዎች ግንዛቤ በሰጠ መንገድ የገንዘብ ማሰባሰብ ሊያካሂድ፣ ገንዘብ ሊበደር እና ክፍያዎችን ሊፈጽም ይችላል፡፡

5. ማኅበሩ የእዳ መግለጫ ሠነዶችን ሊያወጣ የሚችል ቢሆንም ይህ ተፈጻሚ የሚሆነው በማኅበሩ አባላት ልዩ እግድ ሲሰጥ ብቻ ይሆናል፡፡

6. ማኅበሩ ከሌሎች ድርጅቶች እና ሰዎች ጋር ሕጋዊ ስምምነቶችን ሊፈጽም ይችላል፡፡

ምዕራፍ አሥር

ስለ ኦዲት

ክፍል 23

1. የማኅበሩ የሒሳብ መዛግብትና ሬከርዶች (እ.ኤ.አ. መጋቢት 31 ለሚጠናቀቀው የበጀት ዓመት) በገለልተኛ ኦዲተር ተመርምረው የተሟላ የፋይናንስ መግለጫ ለዓመታዊ የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ይቀርባል፡፡

2. የጋራ ስብሰባው (እንደአስፈላጊነቱ) አባላትን በኦዲት ሥራ ላይ በጊዜያዊነት በመመደብ የኦዲት ሪፖርት ለጠቅላላው ጉባኤ እንዲቀርብ ሊያደርግ ይችላል፡፡

3. ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ለሚከናወን የኦዲት ሥራ ገለልተኛ ኦዲተር መሾም የማይቻል መሆኑን ካስረዳ በጋራ ስብሰባ የተመረጡ አባላት የበጀት ዓመቱን ኦዲት በማካሄድ የሒሳብ መግለጫ ለጠቅላላ ስብሰባው ያቀርባሉ፡፡

4. ገለልተኛ የሆነ ዲተር (ከላይ በክፍል 23(3) የተገለጸው ሲያጋጥም) በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ የሒሳብ ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

5. አባላት የማኅበሩን የሒሳብ መዛግብትና ሬከርዶችን ተቀባይነት የሚኖረው ምክንያት በማቅረብ መመልከት/መመርመር ይችላሉ፡፡

6. የቦርድ እና የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት በሥራ አስፈጻሚው የወጣውን የአፈጻጸም ቅደም ተከተል ሥርዓትን በመጠበቅ የማኅበሩን የሒሳብ መዛግብትና ሬከርዶችን በማንኛውም ጊዜ ማግኘት ይችላሉ፡፡

ምዕራፍ አሥራ አንድ

ካሣ ስለመክፈል

ክፍል 24

ለማኅበሩ ዓላማ ተፈጻሚነት በታማኝነት ኃላፊነት በመውሰድ በአስተዳደር፤ በማኅበራዊና በወንጀል መከላከል ሁኔታዎች ግዴታውን ለተወጣ በሥራ ላይ ላለ/ለነበረ አባል ካሣ ይከፈላል፡፡

ምዕራፍ አስራ ሁለት

የማኅበሩ መፍረስ

ክፍል 25

1. ማኅበሩ በማኅበረሰብ እና በአልበርታ ክፍለ ግዛት ቢዝነስ ኮርፖሬሽን ሕግ መሠረት ሊፈርስ ይችላል፡፡ ማኅበሩ ሊፈርስ የሚችለው ቦርዱ በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ለአባላት በሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ ሲጸድቅ ብቻ ይሆናል፡፡

2. ቦርዱ ማኅበሩን ስለማፍረስ የውሳኔ ሐሳብ ለጠቅላላ ጉባኤው ከማቅረቡ ቢያንስ ከ30 ቀናት በፊት ለአባላት የጽሑፍ ማስታወሻ (በተመዘገበ ፖስታ) በአድራሻ መላክ ይኖርበታል፡፡

3. ማኅበሩን የማፍረስ ፍላጎትንና የውሳኔ ሐሳብ የያዘ ጽሑፍ አባላት መጨረሻ በነበራቸው አድራሻ የሚላክ ሲሆን ከተላከ በአምስት ቀን በኋላ አባሉ እንደደረሰው ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

4. ማኅበሩን ለማፍረስ የሚቀርብ የውሳኔ ሐሳብ ለመጽደቅ በጠቅላላው ጉባኤ ከተገኙ አባላት የ95 ከመቶውን ድምጽ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

5. የማኅበሩ መፍረስ ከተጠናቀቀና እዳዎች በሙሉ ከተከፈሉ በኋላ የሚቀረው ንብረት ካናዳ ውስጥ ለተመሳሳይ ዓላማ ለተቋቋሙ የኢትዮጵያውያን ማኅበራት ይከፋፈላል፡፡

6. ቦርዱ የፈረሰው ማኅበር ንብረት ሊሰጣቸው ይገባል የሚላቸውን ማኅበራት በመለየት ለአባላት ያሳውቃል፡፡

 

ምዕራፍ አስራ ሶስት

የሕገ ማኅበርና የመተዳደርያ ደንብ ለውጥ

ክፍል 26

1. ይህ ሕገ ማኅበርና የመተዳደርያ ደንብ ለዚሁ ዓላማ በተጠራ የአባላት ዓመታዊ/ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ ብቻ ሊሻሻል/ሊለወጥ ይችላል፡፡

2. ቦርዱ እና/ወይም ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በጠቅላላ ስብሰባ ደንብ መሠረት ማሻሻያ ለማቅረብ ማስታወቂያ መውጣት ይችላሉ፡፡

3. አባላት በግል ወይም በቡድን ሕገ ማኅበሩን የማሻሻያ ረቂቅ ካዘጋጁ ያላቸውን ሐሳብ ለማኅበሩ ጸሐፊ/ ለፕሬዚዳንቱ ተከታዩ የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ስብሰባ ከመደረጉ 30 ቀናት በፊት ማቅረብ ይኖርባቸዋል። የማሻሻያው ረቂቅ ለሚቀጥለው የአባላት ልዩ/ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ አጀንዳ ላይ መያዝ ይኖርበታል፡፡

4. በሕገ ማኅበሩና በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ ያልተካተቱ ተገቢ የፖሊሲና የአሠራር ልምዶች ተፈጻሚነት የሚኖራቸው ለማኅበሩ ጥቅም የሚሰጡና በጠቅላላ ጉባኤው ድጋፍ ሲያገኙ ብቻ ይሆናል፡፡

5. ይህ ሕገ ማኅበር እና የመተዳደርያ ደንቡ ማኅበሩ የሚመራባቸው መሠረታዊ ሠነዶች ናቸው፡፡

6. ከዚህ ሕገ ማኅበርና የመተዳደርያ ደንቡ ጋር የማይጋጩ እስከሆኑ ድረስ የአመራር አካላት ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠትና የአሠራር ችግሮችን ለማቃለል የተለያዩ ፖሊሲዎችን ማውጣት ይችላሉ፡፡

 

ምዕራፍ አስራ አራት

በሕገ ማኅበሩ እና በመተዳደርያ ደንቡ መካከል ያለ ግንኙነት

ክፍል 27

1. ማኅበሩ ከዚህ ሕገ ማኅበር ጋር የተያያዘ የመተዳደርያ ደንብ ይኖረዋል፡፡

2. የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ከሕገ ማኅበሩ ጋር እኩል አቅም እና ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

3. የማኅበሩ አባል ይህንን ሕገ ማኅበር እና የመተዳደርያ ደንቡን ማክበር ይጠበቅበታል፡፡

4. ይህ ሕገ ማኅበርና እና ተያያዥ የሆነው የመተዳደርያ ደንብ በጠቅላላው ጉባኤ በመጽደቅ ከሰኔ 13, 2002, ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለ የማኅበሩ ዋና የመተዳደርያ ሠነድ ሆኗል፡፡ ይህ ሕገ ማኅበር ከዚህ በፊት ሥራ ላይ የነበሩትን ሕግጋተ ማኅበር ይተካል፡፡