top of page

በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ማህበር

መረዳጃ ዕድር የውስጥ ደንብ እና መመዝገቢያ ቅጽ

Calgary Ethiopian Community Association

Edir internal rules & Registration Form

 

1. የእድሩ ስም 

 

ዕድሩ “በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ማህበር መረዳጃ ዕድር” በመባል ይጠራል ።

 

2. ተፈጻሚነት

 

ማህበራችን መተዳደሪያ ደንብ እና በዕድሩ የውስጥ ደንብ መሠረት በዕድሩ አባላት በተመረጡ ኑዑሳን ኮሚቴዋች ተፈጻሚ ይሆናል ።

 

3. የዕድሩ ዓላማ

 

1. የዕድሩ አላማ በዚህ ደንብ መሠረት የቀብር ወጪ ለዕድርተኞች የገንዘብ እርዳታ ለመስጠት እና የቀብር አፈጻጸም ስርአቶችን ድጋፍ ለመስጠት የሟች ቤተሰብን ለማስተዛዘን ሲሆን እድሩ የሚያገለግለው ለዕድርተኞች ብቻ ነው ።

2. የእድሩ ሁለተኛው ዓላማ፤ ማሕበረሰቡን በጠቅላላ፤ በተለይ ግን እድርተኞችን፤ ሞት ለሰው ልጅ የማይቀር በመሆኑ፤ ቅድመ ዝግጅት የሚያስፈልግ መሆኑንና ስለ ኢንሹራንስና ስለ ኑዛዜ አስፈላጊነት የበለጠ ለማሳወቅ ነው።

 

3. የዚህ ደንብ ግብ በካልጋሪ እና አካባቢው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወቅታዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ በካልጋሪ ኢትዮጵያውያን ማህበር ሥር የሚዋቀር እድር ማቋቋምና ዕድሩ የሚያስፈልገውን ደንብ ፤ አወቃቀር፤ ተግባሮችን እና ሀላፊነቶችን እንዲሁም አመራርን ለመወሰን ነው ።

 

4. የእድሩ ጥቅም

 

1. ለቀብር ወጪ የሚከፈለው ገንዘብ መጠን፤ ከዚህ መተዳደሪያ ደንብ ወደፊት በእድሩ ንዑስ ኮሚቴ እና በዕድሩ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጸድቆ በሚሻሻለው ደንብ መሰረት ይከናወናል ። በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ፤ በእድሩ የበላይ ተቆጣጣር ኮሚቴ አማካኝነት፤ ልዩ ልዩ የቀብር አገልግሎቶችንና የሚመለከታቸውን ወጪዎች በዝርዝር አስጠንቶ ተገቢ የሚሆነውን ክፍያ በእድሩ ጠቅላላ ስብሰባ ያጸድቃል ።

2. እድሩ ለሟች ቤተሰብ የሚያቀርበው አገልግሎት፤ በእድሩ የገንዘብ ችሎታ መሠረት የክፍያ መጠን ለሁሉም እኩል በሆነ የእድሩ ጠቅላላ ስብሰባ በወሰነው መመሪያ መሠረት ይከናወናል። እድሩ ከተቋቋመ ወደፊት ሊሻሻሉ የሚችል ሲሆን  ፤ ለእያንዳንዱ ሞት፤ ለቀብር አገልገሎት የሚከፈለው ገንዘብ መጠን መነሻው  $12,000.00 ይሆናል። ቢሆንም፤ በእድሩ የቁጠባ ሒሳብ ያለው ገንዘብ፤ ከእምስት ሟች ከሚከፈለው በታች ሲሆን እድርተኞች አስቸኳይ መዋጮ እድርገው እንዲያሟሉ ይደረጋል ።

3. የሟች ቤተሰብ የማይስፈልገው መሆኑን ካልገለጸ በስተቀር፤ እድሩ ለቀብር በሚያስፈለገውን ዝግጅት በማድረግ እድርተኞችን ይረዳል ። ይህ ሃላፊነት የሚክናወነው፤ እድርተኞችን በዓመት በሙሉ በየሳምንቱ ተራ በማስተባበር በማስገባት እድርተኞች እንዲረዳዱ በማድረግ ነው።

 

4. ዕድርተኞች በሁሉም መንገድ ወቅታዊ ዝግጅት እንዲያደርጉ እንዲሁም ኢንሹራንስና ኑዛዜ እንዲኖራቸው በማስተማር ይረዳል።

 

5. ዕድሩ፤ እንደ አስፈላጊነቱ፤ ልዩ ልዩ የቀብር አገልግሎቶችን እያጠና ተቀባይነት ያለውና በወጪውም መጠነኛ የሆነ አገልግሎት በማቅረብ የዕድርተኞች ቁጥር ከፍ እንዲልና እድሩም በገንዘብ ረገድ ተጠናክሮ ለእድርተኞችም የተሻለ ጥቅም እንዲያስገኝ ሐላፊነት አለበት።

 

5. ዕድርተኛነት

1. ማንኛውም በካልጋሪ እና አካባቢው ቋሚ ነዋሪ የሆነ እድሜው ቢያንስ ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ የካልጋሪ ማህበረሰብ ማህበር አባል የሆነ እድርተኛ መሆን ይችላል ።

 

2. እድሩ በኢትዮጵያውያን መሀል በዘር በሃይማኖትና በጾታ ልዩነት እንዲሁም የፓለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይመለከት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በዕኩልነት ያገለግላል ። 

 

3. ማንኛውም እድርተኛ የአባልነት ክፍያውን ከታች በተዘረዘረው መስፈርቶች መሰረት አሟልቶ መክፈል አለበት ።​

(ሀ)  ዕድርተኛው ቤተሰብ እራሱ ባል ወይም ሚስት እንዲሁም አንድ ወደ ላይ እና አንድ ወደታች የሚዛመድ (እናት ወይም አባት እንዲሁም ልጆችና የጉድ ፈቻ የአሳዳጊነት ሞግዚት ስልጣን በህግ የተረጋገጠ ማስረጃ ያለው ልጁ ቤተሰብ ሲመዘገብ በአመት የሚከፍለው የገንዘብ መጠን $ 320 የካናዳ ብር ይሆናል :: ይህ የዕድሩ አባል በቤተሰቡ ላይ ሞት ሲያጋጥም የሚከፈለው ክፍያ መጠን $ 12,000.00 የ ካናዳ ብር ይሆናል ::                                                                                                                                                                                                             

(ለ ) ዕድርተኛው ትዳር የሌለው ከሆነ እና በስሩ የሚያስተዳድራቸው ልጆች ያሉት (ነጠላ ቤተሰብ የሆነ) እንዲሁም በህግ የተረጋገጠ የአሳዳጊነት ሞግዚት ስልጣን የተሰጠው ልጅ ያለው እና የእድርተኛው ወላጅ እናት እና አባት ጨምሮ የተመዘገበ እድርተኛ አባል በአመት የሚከፍለው ክፍያ መጠን $ 240 የካናዳ ብር ይሆናል:: ይህ የእድር አባል በቤተሰቡ ላይ ሞት ሲያጋጥም የሚከፈለው ክፍያ መጠን $ 12,000.00 የካናዳ ብር ይሆናል ::

(ሐ) ትዳር የሌለው እሱ ካለፈ በኋላ ለጓደኞችና ለዘመድ ችግር ጥሎ ለማለፍ የማይፈልግ የዕድር አባል በአመት ክፍያ መጠን - $ 180 የካናዳ ብር በመክፈል የዕድሩ አባል መሆን ይችላል ::

(መ) ሁለት ወይም ከዛም በላይ የሆኑ ተመሳሳይ እናት እና አባት ያላቸው የዕድሩ አባላት እናት ወይም አባት በሚያርፍበት ጊዜ የሚከፈለው ጥቅም በአረፈው ግለሰብ እንጂ በአባላት ብዛት ልክ አይደለም የሚከፈለውም የገንዘብ መጠን $ 12,000.00 የካናዳ ብር ይሆናል ::

(ሠ) የዕድርተኛው ወላጅ እናት ወይም አባት ያረፉት ከካናዳ ውጪ ከሆነ የሚከፈለው የክፍያ ገንዘብ መጠን $ 6000 የካናዳ ብር ይሆናል ::

4. አንድ የእድሩ አባል፤ ከ 18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ያለበት ቤተሰብ ወይም 18 ዓመት እድሜ የደረሰ ቀደም ሲል በንዑስ ቁጥር 5.3 ላይ የተገለጸውን ክፍያ በየአመቱ በወቅቱ እንዲከፍል ይጠበቅበታል። ክፍያውን ለማጠናቀቅ እድርተኛው በሦስት ወር ጊዜ ገደብ ክፍያውን እንዲያጠናቅቅ ይሰጠዋል። እድርተኛው በተመደበለት ጊዜ ገደብ ውስጥ ክፍያውን ካላጠናቀቀ፤ በእድር አባልነት የመቀጠል ፍላጎት እንደሌለው ተቆጥሮ ከአባልነት መዝገብ ይሰረዛል :: የእድርተኛ መብቱንና ጥቅሙን በሙሉ ያጣል። እድርተኛውን ስለ ክፍያው የአደራ ደብዳቤ የተላከለት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ ማካተት አለበት።

5. ማንኛውም አዲስ ተመዝጋቢ እድርተኛ የእድሩ ተጠቃሚ የሚሆለው በአባልነት ከተመዘገበ ከሦስት ወር የቆይታ ጊዜ በኋላ ነው።

6. አንድ ዕድርተኛ በእድሩ ደንብ በጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የቤተሰቡን አባላት ሙሉ መረጃ በዕድሩ መመዝገቢያ ቅፅ ማስመዝገብ እና ጠቃሚ ሰነዶችንም ማካተት አዲስ የቤተሰብ አባል ሲኖርም በወቅቱ በማስመዝገብ ሙሉ ሐላፊነቱን መወጣት የእድሩ አባል ግዴታ ነው ።

7. ዕድርተኝነት ተላልፎ ለሌላ ሰው የማይሰጥና በውርስ የማይተላለፍ ነው።

8. የዕድርተኛው ባለቤት በሞት ቢለይ በሕይወት ያለው ባለቤት በየአመቱ የተመደበለትን ክፍያ እየከፈለ በመቀጠል ዕድርተኛ አባል ሆኖ መቀጠል ይችላል።

9. ማንኛውም እድርተኛ በማንኛውም ግዜ ከእድሩ የመውጣት መብት አለው። እድሩን የሚለቀው እድርተኛ ቀደም ብሎ ከከፈለው ክፍያ ምንም አይነት ገንዝብ እንዲመለስለት የመጠየቅ መብት የለውም፤ ምንም አይነት ተመላሽ ገንዘብም አይሰጠውም።

10. ማንኛውም የእድሩ አባል ቀደም ብሎ በእድሩ ቅጽ ላይ ያስመዘገበው የመኖሪያ ቤት አድራሻም ሆነ፣ የስልክ ቁጥር እና ኢሜል ቢቀይር  በጽሁፍ የማሳወቅ የእድርተኛው ሃላፊነት ነው።

11. ማንኛውም የዕድሩ አባል በምርጫ ወቅቶች እና የአባላት ጠቅላላ ስብሰባ በሚኖርበት ጊዜ የመገኘትና ሃሳብ የመስጠት፣ የእድሩን ሐላፊዎች የመምረጥና በእጩነት ቀርቦ የመወዳደር መብት አለው። ይህንን ለማድረግ የዕድሩ ዋና አባል መሆን አለበት።

12. የዕድሩ አባል የነጠላ ቤተሰብ ሲኖረው እና አንድ የቤተሰብ አባል የሆነ የትዳር ፍቺ ሲያጋጥመው ወዲያውኑ ለዕድሩ አሳውቀው ሁለቱም በነጠላ ቤተሰብ ምዝገባ እና ክፍያ መጠን በመክፈል የነጠላ ቤተሰብ ዕድርተኛ አባል በመሆን ጥቅሞችን ማስቀጠል ይችላሉ ።

6. የእድርተኞች ምዝገባ

ማንኛውም እድርተኛ የማመልከቻውን ቅጽ መሙላት እና አመታዊ ክፍያውንም በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ መከፈል ይኖርበታል። እንዲሁም፤ የካልጋሪ እና አካባቢው ነዋሪ መሆንን ማረጋገጪያ መታወቂያ ካርድ ወይንም ሌላ ህጋዊ መረጃ ማቅረብ ያኖርበታል ። እድርተኛ የመመዝገቢያ ፎርሙን ሲሞላ የሚሞላቸው ነጥቦች በሙሉ ትክክል መሆን አለባቸው። ይህ ካልሆነ ንዑስ ኮሚቴው ይህንን ግለሰብ ከእድሩ የማገድ መብት አለው።

7. የዕድሩ አወካከል እና የምርጫ ሥርዓት

1. በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ማህበር የተዋቀረው የኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብን ለማገልገል ሲሆን፤ ዕድሩ የሚተዳደረው በዕድሩ አባላት በምርጫ በተመረጡ በንዑስ ኮሚቴ ተመራጮች አስተዳደር ሐላፊነት ብቻ ነው ። ተመራጮች የንዑስ ኮሚቴውን ተግባሮች በሙሉ የሚያከናውኑ ሲሆን በሚከተሉት የሥራ ሐላፊነት ተመራጮችን ያካትታል ። ሊቀመንበር፣ ጸሐፊ፣ የሂሳብ ተቆጣጣሪ፤ ገንዘብ ያዥ እና ሕዝብ ግንኙነት ሲሆኑ በአጠቃላይ አምስት ንዑስ ኮሚቴ ተመራጮች የተዋቀረ ይሆናል ።

2. እድሩን በተመለከት፤ የዚህ እድር የአመራር ተዋረድ እንደሚከተለው ይሆናል።

(ሀ) የንዑን ኮሚቴው ተመራጮች ተጠሪነታቸው በዕድሩ ጠቅላላ ጉባዔ ይሆናል፤

(ለ) የካልጋሪ ማህበረሰብ ማህበር ሥራ አስኪይጅ ኮሚቴ የእድሩ የበላይ ተቆጣጣሪ ጠባቂሆኖ ያገለግላል ።

3. የማህበሩ የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አስመራጭ ኮሚቴ ሆኖ ያገለግላል። አስመራጭ ኮሚቴው፤ ተገቢ የሆኑ የመገናኛ ዘዴዎች ሁሉ በመጠቀም እድርተኞች ጥቆማ እንዲያከናውኑ ይጋብዛል። ኮሚቴው፤ ተጠቋሚዎችን ለሚፈለጉት አገልግሎት ፈቀደኛ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ኮሚቴው የእያንዳንዱን ተጠቋሚ ችሎታ በጥንቃቄ ካጣራ በኋላ ምርጫ ለሚያስፈልገው ለእያንዳንዱ ሥራ ሁለት ሁለት ተጠቋሚ ያለው ዝርዝር ያጠናቅቃል። ከቀረቡት ሁለት ሁለት ተመራጮች አንዱን በመምረጥ ምርጫ ይከናወናል።

4. የአስመራጭ ኮሚቴው በተገኘው የመገናኛ ዘዴ ሁሉ በመጠቀም ለእድርተኞች በሙሉ ስለ እያንዳንዱ ተመራጭ አመር ያለ የሕይወት ታሪክ እና ፎቶግራፍ ያቅርባል።

5. በምርጫው ወቅት በአካል ለመገኘት ያልቻሉ እድርተኞች በተወካይ አማካኝነት በምርጫ መብታቸው ሊጠቀሙ ይችላሉ። ቢሆንም፤ ውክልናውን ያረጋገጡበት እንደ ደብዳቤ፤ ኢሜይል ወይም ፋክስ በጥንቃቄ ይመዘገብና በኋላ በሚመለከተው እድርተኛ እንዲፈረም እደረጋል።

 

6. የማህበሩ የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት ምርጫው ወገንተኛነት በሌለበትና በትክክል መከናወኑን የማረጋገጥ ሀላፊነት አለባቸው።

 

8. የዕድሩ የበላይ ተቆጣጣሪ

 

በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ የእድሩ የበላይ ተቆጣጣሪ ሆኖ ያገለግላል። የዚህ ኮሚቴ ዋነኛ ተግባሩ የዕድርተኞችን ጥቅም ማስጠበቅ ይሆናል። ሊፈጠሩ በሚችሉ የተለያዩ የእድሩ የበላይ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊንት፤

1. ከእድሩ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለእድሩ ስራ መቃናት የሚረዳ የአሰራር ዘይቤዎችን እና ዘዴዎችን፤ ፖሊሲ እንዲሁም የእድሩን እመታዊ በጀት በመተለም እና በማዘጋጀት ለጠቅላላ የእድሩ ጉባኤ መቅረቡንና መጽደቁን ያረጋግጣል።

 

2.በእድሩ ደንብ መሠረት የእድሩ ንዕስ ኮሚቴ ተመራጮች በትክክል እየተተገበሩ እና በሥራ ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ያረጋግጣል።

 

3.የእድሩ ገንዝብ ነክ ጉዳዮች እውነተኛና ትክክለኛ የአስራር ዘዴ የተከተሉ መሆናቸውን ያረጋግጣል።

 

4.በማንኛውም ጊዜ በእድሩ ተዋረድ እርከን አባላት ወይንም አካላት መሃል ያለመግባባት ቢፈጠር በሀገራዊ የሽምግልና ዘዴ፣ በበሰለ እና በሰከነ ሁኔታ ነገሮችን ተመልክቶ ችግሮችን የመፍታት እና መልካም ግንኙነትን በአባላት መሀከል የመፍጠር ሃላፊነት አለበት።

 

5. በእድሩ ጠቅላላ ጉባኤ ከተወሰነው የዓመት በጀት 10% (አስር ፐርሰንት) ያልበለጠ የወጪ ጥያቄ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተጠንቶ ሲቀርብለት ወጪውን ካመነበት የመፍቀድ ስልጣን አለው።

6. ከዚህ በላይ በ8.5 የተጠቀሱት የወጪ ገደቦች በቀብር ማስፈጸሚያ በዚህ ደንብ ላይ እንዲክፈል የተወሰነውን ክፍያ ለመፈጸም የሚወጣን ወጪ አይመለከቱትም።

 

7. በእድሩ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የንሁስ ኮሚቴ ሪፖርት ትክክለኛነትን ማረጋግጥ፤

 

8. ከሂሳብ ተቆጣጣሪው ጋር በቅርብ በመስራትና በመተባበር የሂሳብ ተቆጣጣሪውን ሪፖርት መረዳትና መልሶ ለእድሩ አባላት ማስረዳት መቻል፣ እንዲሁም ክሂሳብ ተቆጣጣሪው የሚሰጥ የባለሙያ ምክርና የተሻሻለ የአሰራርን ስሌት በእድሩ ውስጥ ተፈጻሚ ሆኖ በተግባር እንዲተረጎም ማድረግ።

 

9. ከእድሩ ንዕስ ኮሚቴ ባግባቡ ተሰርቶ በቀረበለት የገንዘብ መጠየቂያ ፎርም መሰረት ቼክ ያዘጋጃል።

 

10. ማንኛውም ገንዘብ መሰብሰብ እና ክፍያዎች የሚካሄደው በማህበሩ ጽ/ቤት እና የመፈረም አላፊነት ባለባቸው የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ኣባላት ይሆናል።

 

9. የሂሳብ መርማሪ

 

1. የእድሩ ሂሳብ መርማሪ በእድሩ ጠቅላላ አባላት ለሶስት አመት የስራ ዘመን ይመረጣል። የሂሳብ መርማሪው ለማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ እና ለእድሩ ጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት ያቀርባል።

 

2. በየአመቱ የእድሩ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የአስመራጭ ኮሚቴ ሁለት ለሂሳብ መርማሪ ስራ ብቁ የሆኑ ግለሰቦችን ለምርጫ አቅርቦ የእድሩ አባላት በድምጽ ብልጫ እንዱን እጩ ለድሩ ሂሳብ መርማሪ እድርገው ይመርጣሉ።

 

3. የሂሳብ መርማሪ የሚመረጠው ለሶስት አመት እና እሱን የሚተካው የሂሳብ መርማሪ እስኪመረጥ ድረስ ይሆናል። የሂሳብ መርማሪ በእድሩ አባላት ከተፈለገ እና እሱም ፈቃደኛ ከሆነ በድጋሚ ለአንድ ተጨማሪ ግዜ ተመርጦ ሊያገለግል ይችላል።

 

4. የእድሩ የሂሳብ መርማሪ ሀላፊነት እና የስራ ድርሻ፤

 

(ሀ) የእድሩን፣ የገንዘብ ወጪ፣ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ሀብት ይቆጣጠራል። የስራውንም ግኝት ከካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ እንደዕድሩ የበላይ ተቆጣጣሪ ኮሚቴና ለእድሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ያደርጋል። ማንኛውንም በሒሳብ ሹም በኩል የሚዘጋጁ የሂሳብ ዶክመንቶችን ትክክለኛነታቸውን አርጋግጦ ይፈርምባቸዋል።

(ለ) ከአመታዊ ሪፖርት ባሻገር ለእድሩ የበላይ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ በየስድስት ወሩ የእድሩን የሂሳብ ሁኔታ የሚያሳይ ሪፖርት ያቀርባል።

(ሐ) የሥራ ዘመኑን ፈጽሞ የሚሰናበተውን የእድሩ ንዑስ ኮሚቴ ከመሰናበቱ በፊት የሂሳብ መርማሪው ይህ ኮሚቴ በሃላፊነት ላይ በቆየበት ዘመን የእድሩ የሂሳብ ሁኔታ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ የሚያሳይ ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል። ይህም ሪፖርት ተሰናባች የኮሚቴ አባላት በእድሩ ሂሳብ ላይ ያደረገውን አስተዋጾ በታሪክነት ለመዘገብ ይችላል።

(መ) ከተሰናባቹ የኮሚቴ አባላት ወደ አዲሱ ተመራጭ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚደረገውን ሽግግር የተቀላጠፈ እንዲሆን ያግዛል።

(ሠ) የሂሳብ መርማሪ ማንኛውንም የእድሩን ሂሳብ የሚያሳዩ ዶክመንቶችን ወይንም ኮምፒውተር ለመመልከት የመጠየቅም ሙሉ መብት ያለው ሲሆን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት፤ የእድሩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሂሳብ መርማሪው ስራውን ለማከናወን የሚጠይቃቸውን ሰነዶች በወቅቱ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው።

(ረ) በ(ሠ) በተመለከተው መሰረት ሰነዶች ሲጠየቁ በፊርማ መረከብና በኋላም በአግባቡ ተጠቅሞ በሰዓቱ ሰነዶችን መመለስ ግዴታ አለበት።

10. የእድሩ ንዑስ ኮሚቴ

የእድሩ ንዑስ ኮሚቴ 4 አባላት ይኖሩታል። አንድ በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል ሲሆን የተቀሩት በሊቀመንበርነት፣ በጸሐፊንት፣ በሂሳብ ሹምነትና፣ በማህበራዊ ጉዳይ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው።

1. በእድሩ ድንብ መሠረት የእድሩን ፖሊሲ፣ በጀት፣ እቅድ እና በጥቅል የእድሩን ደንቦች በሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል።

 

2. የእድሩ ሥሩ የእድሩን ደንብ ተከትሎ በተቀላጠፈ እና ፍሬያማ በሆነ ሁኔታ እንዲካሄድ ያድርጋል።

3. ወርሀዊ፣ የሶስት ወር፣ የስድስት ወር እና የአመት ሪፖርት ለካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ እና ለእድሩ ተቆጣጣሪ ያቀርባል።

4. ለሥራ ቅልጥፍና እንዲያመቸው የእድሩን ደንብ እማይቃረን የራሱ የውስጥ የሥራ መመሪያ አውጥቶ ይሠራል። ማናቸውንም አዲስ የስራ መመሪያ ለበላይ ተቆጣጣሪ ያሳውቃል።

5. ግልጽ የሆነ ወጪ እና ገቢን በቀላሉ የሚያሳይ እና በማንኛውም ሰአት ለመመርመር የተዘጋጀ የሂሳብ አያያዝ ዘዴን ይዘረጋል።

6. እድሩ የሚያድግበትን እና የሚዳብርበትን ዘዴ እየፈለገ እና እያጠና ለእድሩ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ያቀርባል። እንዱሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጥናቱን ለጠቅላላ የእድሩ ጉባኤ ያቀርባል።

7. ማናቸውንም የእድሩ የአለት ከእለት ሥራ በሃላፊነት ይመራል። እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆን ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋም ስራዎችን ያሰራል።

8.የእድሩን ሂሳቦች ያስመረምራል፣ ለሂሳብ ተቆጣጣሪውም የሂሳብ ምርመራውን እንዲያደርግ በሚያስፈልገው ሁሉ ይተባበራል።

9. በጠቅላላ የአባላት ስበሰባ በመጥራት ሂደት ከበላይ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ እርዳታ ወይም ድጋፍ ያደርጋል።

10. በዚህ ንዑስ ኮሚቴ ስር ተመርጠው የሚያገለግሉ አባላት ላገለገሉበት ዘመን ከእድሩ አመታዊ ክፍያ ነጻ ይሆናሉ።

11. የእድሩ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ኅላፊነት

 

1. የእድሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር በእድሩ ጠቅላላ አባላት ለሦስት አመት የስራ ዘመን ይመረጣል።

2. ለእድሩ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ሪፖርት ያደርጋል።

3. በእድሩ አባላት ከተፈለገ እና እሱም ፈቃደኛ ከሆነ በድጋሚ ለአንድ ተጨማሪ ግዜ ተመርጦ ሊያገለግል ይችላል።

4. በእድሩ የተቆጣጣሪ ኮሚቴ ሥር ሆኖ እድሩን በበላይነት ይመራል፤ ይስተዳድራል።

5. እድሩን የወደፊት አካሄድ ይገመግማል፣ የእድሩን በትክክለኛ መንገድ መጓዙን ያረጋግጣል።

6. በዚህ መተዳደሪያ ደንብ እና በጠቅላላ ጉባኤ ወይም ንዑስ ኮሚቴው በሚሰጠው መመሪያ መሰረት እድሩን በሚመለከት በማንኛውም ጉዳይ እድሩን ወክሎ ይናገራል። አስፈላጊውን ግንኙነት ሁሉ ይፈጥራል።

7. የንዑስ ኮሚቴ ስብሰባዎችን በሊቀመንበርነት ይመራል።

8. ለንዑስ ኮሚቴ አባላትም ሆነ ለማንኛውንም የእድሩ አባል የመልካም ባህሪ ምሳሌ መሆን ይጠበቅበታል።

12. የእድሩን ንዑስ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ

1. የእድሩን ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ በእድሩን ጠቅላላ አባላት ለሦስት አመት የስራ ዘመን ይመረጣል።

2. ለሊቀመንበር ሪፖርት ያደርጋል።

3. በእድሩን አባላት ከተፈለገ እና እሱም ፈቃደኛ ከሆነ በድጋሚ ለአንድ ተጨማሪ ግዜ ተመርጦ ሊያገለግል ይችላል።

ዋና ጸሐፊ ሃላፊነት እና የስራ ድርሻ፤

(ሀ) የእድሩ አባላት በሚመለከት ዘገባ ይይዛል።

(ለ) እድሩን የሚመለከቱ ዶክመንቶችን፣ ፎርሞች እና መዝገቦች በተዘጋጀለት ማህደር ውስጥ መቀመጣቸውን ያረጋግጣል።

(ሐ) ማንኛውም አባላት አድራሻም ሆነ የሚኖሩትን ለውጦች ለጽ/ቤት በማስታወቅ ተክክለኛነታቸውን ያረጋግጣል።

(መ) ለእድርተኛን ሆነ ለሌላ አካል እድሩን በሚመለከት ላለው ጥያቄ ሁሉ በማዳመጥ ሲቻልም መልስ በመስጠት አለበለዚያም ጉዳዩን ለኮሚቴ ስብሰባ በማቅረብ መፍትሔ ይሻል።

(ሠ) በዋናው የእድር መዝገብ ላይ የአባላትን ስም ዝርዝር እና አድራሻ በትክክል መያዙን ያረጋግጣል።

(ረ) የንዑስ ኮሚቴውን ስብሰባ እና የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ አጀንዳ በማዘጋጀት ሊቀመንበሩን ይረዳል።

(ሰ) የእድሩን ጠቅላላ ጉባኤውና የንዑስ ኮሚቴ ስብሰባዎችን ቃለ ጉባኤ ይይዛል። በሥርዓትም ያስቀምጣል።

(ሸ) በአጭር ግዜ የእድሩ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር በሌለበት ግዜ እንደ የእድሩ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ ጉዳዮችን ያከናውናል።

(ቀ) በእድር ጠቅላላ ጉባኤውንና የንዑስ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ የእድሩ ደንብ የሚጠይቀው የስብሰባ ምልዓተ ጉባኤ በትክክል መሙላቱን ያረጋግጣል።

(በ) አስፈላጊ ሲሆን ለማንኛውም የእድሩ ነክ በሆነ ጉዳይ የእድሩን አባላት ያነጋግራል።

13. ገንዘብ ያዥ

                                                                            

የካልጋሪ እና አካባቢው መረዳጃ እድር ንዑስ ኮሚቴ ገንዘብ ያዥ ይሆናል።

 

1. ማንኛውንም የእድሩን ገቢ በደረሰኝ ይቀበላል።

2. በደረሰኝ የተረከበውን የእድሩ ገቢ በእድሩ ስም በተከፈተው የባንክ ሒሳብ ወይም አካውንት በእድሩ ስም ባንክ ያስገባል።

3. በገንዘብ ያዥነቱ ስላከናውናቸው ተግባራትና ስለእድሩ የገንዘብ አቋም ለእድሩ ኮሚቴ ሊቀመንበርና የተቆጣጣሪ ኮሚቴ ወርሃዊ ሪፖርት ያቀርባል። ይህ ሪፖርት በየወሩ ከባንክ የሚላከውን የእድሩን የባንክ ሂሳብ የሚያሳየውን ዶክመንት  ይጨምራል። እንዱሁም ዶክመንቱን የሚመለከት ጥያቄን ይመልሳል። ይሄ ወርሐዊ ሂሳብ ዶክመንት ሪፖርት ኮፒ ተደርጎ በእድሩ ሰነድ ውስጥ ያስቀምጣል።

4. ወጪ መጠየቂያ ፎርም ተሟልቶ ሲመጣለት ቼክ በማዘጋጀት እና የመፈረም ኃላፊነት ባለባቸው ተመራጮች አስፈርሞ ወጪ ያደርጋል።

የሚከተሉትን የእድሩን ደንቦች መከበራቸውን ያረጋግጣል ወይንም ያከናውናል።

(ሀ)በእድሩ ደንብ መሰረት የተፈቀደ ወጪ ሁሉ መጀመሪያ በእድሩ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ታይቶ መፈቀዱን ማረጋገጥ። ማንኛውም ከእድሩ የባንክ ሂሳብ የወጪ ጥያቄ በእድሩ ሊቀመንበርና ሂሳብ ሹም መፈረም አለበት።

(ለ) የባንክ ወጪ ሰነዶችን ግልባጭ ለእድሩ መርማሪና ይሰጣል፣ በእድሩ ፋይል ይቀመጣል።

(ሐ) ማንኛውም እድሩን የሚመለከት ዶክመንቶች ለእድሩ ተመራጮች በማናቸውም ጊዜ ያቀርባል።

14. የሂሳብ ሹም

የእድሩ ሂሳብ ሹም በእድሩ ጠቅላላ አባላት ለሶስት አመት የስራ ዘመን ይመረጣል። የእድሩ የሂሳብ ሹም በእድሩ አባላት ከተፈለገ እና እሱም ፈቃደኛ ከሆነ በድጋሚ ለአንዴ ተጨማሪ ግዜ ተመርጦ ሊያገለግል ይችላል። የእድሩ ሂሳብ ሹም ለሊቀመንበር ሪፖርት ያደርጋል። የእድሩ የሂሳብ ሹም ሀላፊነትና የስራ ድርሻ፤

1. የእድሩ አመታዊ በጀት በትክክል በእድሩ ጉባኤ እና በእድሩ ድንብ መሰረት በሥራ ላይ እየዋለ መሆኑን ያረጋግጣል።

2. የእድሩን ሂሳብ በጥንቃቄ ይይዛል።

3. የእድሩን የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረት ወይም ገንዘብ ገቢና ወጪ በዘመናዊ የሂሳብ አያያዝ ዘዴን በመከተል መዝገብ ይይዛል። የመዝገቡንም ትክክለኛነት ያረጋግጣል።

4. በየጊዜው የሚሰበሰብን የእድሩን ገንዘብ በወቅቱ ባንክ መዝጋቱን ይቆጣጠራል። ገቢ የሆነበትንም ሰነድ ኮፒ ከእድሩ ገንዘብ ያዥ ተቀብሎ ያስቀምጣል፤ ሂሳብንም በትክክል ይመዘግባል።

5. የሚቀርቡለትን ዶክመንቶች ወይንም ደረሰኞች ትክክለኛነት ያረጋግጣል።

6. ወርሀዊ፣ በየሦስት ወሩ እንዲሁም አመታዊ በተጨማሪም በእድሩ የበላይ አካል በተጠየቀ ጊዜ ስለ እድሩ የገንዘብ አቋም ሪፖርት ያቀርባል።

7. በደንብ የተፈቀደ ወጪ ሲያጋጥም የወጪ ማዛዣ አዘጋጅቶ ለሊቀ መንበሩ አቅርቦ ያስፈርማል፤ ስለሂሳብ ትክክለኛነት እርሱም በፊርማው ያረጋግጣል።

8. በማንኛውም ሰአት ለሂሳብ ተቆጣጣሪው ዶክመንቶችን በመስጠትም ሆነ የሂሳብ ተቆጣጣሪው ለሂሳብ ምርመራ የሚፈለገውን ማቅረብ መቻል ይኖርበታል።                                                                                                                            

 

9. የእድሩን ጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ያቀርባል።

15. ማህበራዊ ጉዳይ ሐላፊ

1. የዕድሩ ማህበራዊ ጉዳይ ተጠሪ ሐላፊነት ስለ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር እና ዕድሩ ያላቸውን  ህብረት እና አንድነት የጋራ ጥቅሞች ስለ እድሩ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ለካልጋሪ እና አካባቢው ለሚገኙ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ማስተዋወቅ እና ግንዛቤ ማስጨበጥ ይኖርበታል።

2. የእድሩ አባላት ለሆኑና አባል መሆን ፍላጎት ላላቸው ስለሀዘን ጊዜ ስለሚደርስ መንፈሳዊና ቁሳዊ ችግሮች ማብራሪያ መስጠትና አስፈላጊ ሲሆን በራሪ ፅሁፎችን በማዘጋጀት እንዲሰራጭ ያደረጋል።

3. የእድር አባል ሀዘን ሲደርስበት ከአባላት መሀል ቡድን አዋቅሮ ሀዘንተኛውን የሚያስፈልጉትን ማህበራዊ ድጋፍና ዝግጅት ያስተባበራል።

 

4. የእድር አባል ሀዘን ሲደርስበት ለአባላት  ስለቀብር  መርሀግብር ለአባላቱ ማሳወቅ እና እንዲገኙ ያሳስባል።

5. እድርትኛ መርዶ የተቀመጠ ከሆነ አድራሻና ስልክ ቁጥርን ለአባላት ማሳወቅና ሃዘንተኛውን እንዲያፅናኑ ያበረታታል።

 

6. ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር ማህበራዊ ጉዳይ ተጠሪ ጋር ለእድሩ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት ይሰራል።

 

16. የእድሩ ስብሰባ ስነ ሰርዓት

1. በአመት ቢያንስ አንዴ የእድሩ ጠቅላላ ስብሰባ ይኖራል።​

2. የማንኛውም የእድሩ ስብሰባ ምልዓተ ጉባኤ፣ ለስብሰባው እንዲመጡ ጥሪ ከቀረበላቸው ጠቅላላ አባላት ከግማሽ በላይ ሲገኙ ነው።

3. የአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሲያስፈልግ ንዑስ ኮሚቴው በማሳወቅ ብቻ ስብሰባውን መጥራት ይችላል ። የዚህም አስቸኳይ ስብሰባ ምክንያት፤ እንዲሁም ቦታ እና ሰአት ለእያንዳንዱ የእድር አባል በስልክም ሆነ በደብዳቤ ወይንም በተገኘው የመገናኛ ዘዴ ቀደም ብሎ መገለጽ ይኖርበታል። የዚህ አስቸኳይ ስብሰባ ምዕላተ ጉባዔ ከጠቅላላ የእድሩ አባላት 1/2 ወይንም 50% ሲገኙ ነው። ይህ የአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ከተጠራ እና ምልአተ ጉባኤው ካልሞላ ሌላ ስብሰባ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይጠራል። በሁለተኛው ስብሰባ ምላተ ጉባኤ ባይገኝም ስብሰባው እንደተሟላ ተቆጥሮ ከተገኘው አባላት በብዙሀኑ የተደገፈው ሀሳብ የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ሆኖ ይፅድቃል።

4. በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር ለእድሩ ሥራ ቅልጥፍና ይጠቅማል ብሎ ያመነባቸውን የእድሩን ደንብ የማይቃረኑ የውስጥ የአስተዳደር መመሪያዎችን አውጥቶ በስራ ላይ ሊያውል ይችላል። ነገር ግን በጠቅላላ ጉባዔ የጸደቀውን መመሪያ ወይም ደንብ የሚቃረን ከሆነ መጀመሪያ የእድሩ ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ በእድሩ ጉባኤ መጽደቅ ይኖርበታል።

17. የህይወት ዋስትና እና ኑዛዜ

በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር እድር እንደ አላማው የእድሩን አባሎች የሕይወት ዋስትናን እና የወቅታዊ ኑዛዜን ጠቃሚነት ማስታወስ እና በነዚህ ጊዳዮች ዙሪያ አባላቱ በቂ ግንዛቤ አግኝተው ቤተሰባቸውን በክፉ ጊዜ ከሚመጡ በርካታ ችግሮች ማዳን እንዲችሉ በየጊዜው ማስገንዘብ ነው። የእድሩ ንዑስ ኮሚቴ ማህበራዊ ጉዳይ ይህንን የሥራ ዘርፍ ለመወጣት በቂ እውቀት ያለውን ፈቃደኛ ግለሰብ ፈልጎ ይመድባል፤ ሥራውም መሰራቱን ያረጋግጣል።

18. ጠቅላላ የሂሳብ ስራ እና ተጠያቂነት

1. በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ እንደ የእድሩ የበላይ ተቆጣጣሪ የእድሩ የገንዘብን አመታዊ የሂሳብ ሪፖርት ትክክለኛ እና እውነተኛ መሆኑን የማረጋገጥ ሙሉ ህጋዊ ሃላፊነት አለባቸው። ሪፖርቱም ዘመናዊ የሂሳብ ሪፖርት አሰጣጥን ተከትሎ የተሰራ በማድረግ በእድሩ ገንዘብ አያያዝ ዙሪያ ጠንካራ አመራር እንዳለ በማሳየት የእድርተኛውን ሙሉ እምነት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት።

 

2. በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ እንደ የበላይ ተቆጣጣሪነት፤ የእድሩ ንዑስ ኮሚቴ አባላት፤ እና በእድሩ ሂሳብ ተቆጣጣሪ እንዲሁም በጠቅላላ የእድሩ አባላት መሀል መከባበር እና መተሳሰብ ያለበት ግንኙነት እንዲኖር ይጠበቃል። የዚህ አይነቱ እንደምሳሌ የሚጠቀስ ግንኙነት የአባላትን በእድሩ እድገት ተነሳሽነት የተመራጮችንም ሙሉ የስራ ፍቅር እና ፍሬያማነት ይጨምራል።

 

3. የእድሩ አባላት በሙሉ የአመታዊውን ሂሳብ ሪፖርት አንድ ኮፒ እንዲደርሳቸው ይደረጋል። ይህንን እና የመሳሰሉትን ተግባሮች በማከናወን በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ የዚህን እድር ጥንካሬ እንዲገለገሉና በተለይም በገንዘብ አያያዝ ያለውን ጠንካሪ ዲሲፕሊን ለመላው የእድሩ አባላት ማሳየት ይጠበቅበታል።

 

4. በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ እና የእድሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የእድሩ ሂሳብ አካል የሆነውን የእድሩን ንብረት መንካባከብ እና በጥንቃቄ መያዙን የማረጋገጥ ሃላፊነት አለባቸው።

19. የእድሩ ስነሥርዓት

የእድሩ የንዑስ ኮሚቴ፡ የእድሩ ሥራ እንቅፋት ሆኗል ብሎ ያመነበት የኮሚቴ አባል ካለ፤ ለበላይ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ይህንን አባል ተገቢውን የፀባይ ማረሚያ ቅጣት እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል። የበላይ ተቆጣጣሪ ኮሚቴውን ጉዳዩን በጽሞና ተከታትሎ እና አጥንቶ በርግጥም ቅጣትን አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል። ነገር ግን የእድሩ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ እንዲወስዱለት የጠየቀው እርምጃ አንድ በሕዝብ የተመረጠ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልን በእድሩ ሥራ እንቅፋት በመሆኑ ምክንያት ከተመደበበት ሥራ ማባረር ከሆኑ፤ በካልጋሪ የኢትዮጵያውያን ማህበር የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት በጉዳዩ ላይ ድምጽ ሰጥተውበት አባላቱ በሙሉ መቶ በ መቶ በሆነ ድምጽ ሲሆን ብቻ ነው ::  የማህበሩ እርምጃ ሊወሰድ የሚቻለው። ከላይ የተጠቀሰው እርምጃ በተገለፀው መሰረት ተከናውኖ አንድ የሥራ አስፍጻሚ ኮሚቴ አባል ከቦታው ከተነሳ፤ የበላይ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ እና የዕድሩ ንዑስ ኮሚቴ ይህንን አባል እስከሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ የሚተካው ግለሰብ ፈልጎ በማስቀመጥ የእድሩ ስራ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ያደርጋል ። የበላይ ተቆጣጣሪው ኮሚቴ ይህንን የጎደለ ቦታ ለመተካት የመጀመሪያ አማራጭ አድርጎ የሚወስደው ከተሰናባቹ ግለሰብ ጋር በምርጫ ተወዳድሮ ባላማሸነፉ ሳይመረጥ የቀረውን የእድር አባል ይሆናል።

       

20. የእድሩን ዘመንና መፍረስ

እድሩ ላልተወሰነ ዘመን ይኖራል። እድሩ ሊፈርስ የሚችለው የመፍረሱን ሀሳብ በጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ከእድሩ አባላት ሦስት አራተኛው ወገን ውሳኔውን ሲደግፈው ይሆናል። የእድሩ ገንዘብ እና ንብረትንም በተመለከት የእድሩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በእድሩ አባላት ይወሰናል።

 

21. ስለዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሻሻል

የእድሩን ደንብ ስለማሻሻል በዚህ የእድሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ምንም አይነት ማሻሻል ሊደረግ የሚችለው ጉዳዩ ለእድርተኛው ጠቅላላ ጉባኤው ለውይይት ቀርቦ የጠቅላላ ጉባኤው በድምጽ ብልጫ ማሻሻያውን ሲያፀድቀው ብቻ ነው።

bottom of page